በተለያዩ ዘርፎች አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን በመሰነቅ እየተንቀሳቀሱ ላሉ 500 ወጣቶች ሥልጠና ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ዘርፎች አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን በመሰነቅ እየተንቀሳቀሱ ላሉ 500 ወጣቶች ሥልጠና ሊሰጥ ነው
መንግሥት የፈጠራ ሃሳብ የሰነቁ ወጣቶችን እያበረታታ መሆኑን የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015 (ኢዜአ) ፡- መንግሥት የፈጠራ ሃሳብ የሰነቁ ወጣቶችን እያበረታታ መሆኑን የኢትዮጵያ የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በተለያዩ ዘርፎች አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን በመሰነቅ እየተንቀሳቀሱ ላሉ 500 ወጣቶች ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።
የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሁሴን ሐሰን፤ መንግሥት የፈጠራ ሃሳብ የሰነቁ ወጣቶችን እያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
የወጣቶችን ፈጠራ የማበረታታት ሥራው ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና እና ከአገራዊ ልማት ፋይዳ አንጻር እየታየ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በ2015 ዓ.ም ብቻ ከ900 በላይ ወጣቶች በፈጠራ ሥራ ለመወዳደር መመዝገባቸውን ዶክተር ሁሴን አስታውሰዋል።
በብሩህ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድርም እንዲሁ በአገር አቀፍ ደረጃ ምልመላ ተካሂዶ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልፀዋል።
አሁን የሚሰጠው የሁለት ወራት ስልጠናም በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በሕክምና መሳሪያዎች፣ በግብርና፣ በአገልግሎት እና ሌሎች ዘርፎች የፈጠራ ሃሳቦችን በመያዝ ለሚንቀሳቀሱ 500 ወጣቶች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ለወጣቶቹ የሚሰጠው ሥልጠና ሃሳባቸውን ይበልጥ እንዲያበለጽጉ የድጋፍና ማማከር አገልግሎትን እንደሚጨምር ገልጸው፤ የሰርቶ ማሳያ /ወርክ ሾፕ/ ቦታ ስለመዘጋጀቱም ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸው የተመረጡ ወጣቶች በቡራዩ ልዩ ተሰጥዖ ማበልፀጊያ ማዕከል ለአንድ ወር ሥልጠና የተሰጣቸው መሆኑንም ዶክተር ሁሴን አስታውሰዋል።
ሥልጠናውም ወጣቶቹ የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር በሚችሉበት፣ ፕሮቶታይፕ /የሙከራ ምርት/ እንዲያመርቱ የቢዝነስ ዕቅዳቸውን እንዲያደራጁ ያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት /ፋኦ/ ጋር በመተባበር፤ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የሚያስችሉ ፈጠራዎች በወጣቶች እንዲወጡ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተተገበረ መሆኑንም አክለዋል።
ከዚህ ቀደም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተሻለ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች አወዳድሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ዘርፉን አሁንም እየተፈታተነው ቢሆንም የፈጠራ ሃሳቦችን የሚደግፉ የግል ተቋማት እያደጉ መምጣታቸውንና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መመልከታቸው ቀጣይ ተስፋን ሰንቋል ብለዋል።