ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀኃፊ ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀኃፊ ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015 (ኢዜአ) ፡- ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀኃፊ ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በተለይም ከአረብ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
ዋና ፀሐፊው ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳ በትላንትናው ዕለት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በውይይቱም የኃይማኖት መቻቻልንና ሰላምን ጨምሮ በጋራ ፍላጎቶች በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ያላትን ቦታ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሐረር ከተማ፣ የአል ነጃሺ መስጂድና የሶፍ ዑመር ዋሻ በተባበሩት መንግሥታት የባህል፣ ሳይንስና ትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ እስላማዊ ቅርሶችን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊ መስጂዶችና ሰነዶች ባለቤት ናት ብለዋል።
የዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳ የኢትዮጵያ የኃይማኖት መቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር የረጅም ጊዜ ታሪክን አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ከቋሬሾች ጭቆና ሸሽተው ለመጡ ሙስሊሞች መጠለያ በመስጠት የፈጸመችው ተግባር ታሪክ የማይረሳው መሆኑን ማንሳታቸውም ተመላክቷል።