የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ሁለተኛ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ሁለተኛ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2015(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታውን ከጅቡቲው ፋድ ክለብ ጋር ዛሬ ያደርጋል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በዩጋንዳ በንጄሩ ከተማ ‘FUFA Technical Center Stadium’ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ በመጀመሪያ ጨዋታው የብሩንዲውን ቡጃ ኩዊንስን 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በአንጻሩ የጅቡቲው ፋድ ክለብ በውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።
በማጣሪያ ውድድሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ አንድ ከዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ፣ ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ እና ከጅቡቲው ፋድ ክለብ ጋር መደልደሉ ይታወቃል።
በምድብ አንድ ከቀኑ 7 ሰአት የዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ ጋር ይጫወታሉ።
ካምፓላ ኩዊንስ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው የደቡብ ሱዳኑን ዬ ጆይንት ስታርስን 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የማጣሪያ ውድድሩ አሸናፊ ክለብ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በኮትዲቭዋር አቢጃን በሕዳር ወር 2015 በሚካሄደው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።
ውድድሩ እስከ ነሐሴ 24/2015 ይቆያል።