አምባሳደር ሂሩት ዘመነ የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ሂሩት ዘመነ የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጠየቁ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ)፡- በቤልጂየም፣ኔዘርላንድስ፣ሉክሰምበርግና የአውሮፓ ሕብረት ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቀረቡ።
አምባሳደር ሂሩት በኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከተሰማሩ የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ዛሬ በብራሰልስ ተወያይተዋል።
ቤከንካምፕ፣ዶህለር፣ሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ፣ፍሎሬንሲስ፣ዱሜን ኦሬንጅ፣ ኢንኤልቢኤና ሆርቱስ ሰፕላይስ ኢንተርናሽናል በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ ኩባንያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ የግብርና አታሼ ሜዌስ ብሮወር ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ ኩባንያዎቹ ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ያላትን አቅም እንድትጠቀም ቢከናወኑ ይጠቅማሉ ያሏቸውን ተግባራት በማንሳት ተወያይተዋል።
በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተወካይ ተረፈ ዲዳ በኢትዮጵያ ባለው አሁናዊ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ሂሩት የኩባንያዎቹ ተወካዮች ያነሷቸውን ሃሳቦች ለመጠቀም መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ማቅረባቸውን በብራሰልስ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።