ኢትዮጵያ እና ህንድ በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን የልማትና ኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ምክክር ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ህንድ በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን የልማትና ኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ምክክር ተደረገ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ) ፡- በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ከሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማት ትብብር ኃላፊ አብሂላሻ ጆሺ ጋር የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ ሕንድ በኢትዮጵያ በቴክኒክና ኢኮኖሚ ትብብር የምትተገብራቸውን መርሐ-ግብሮች ማስፋት እንደሚገባ መገለጹን ኢዜአ በኒው ዴልሂ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1950 ነው።
አገራቱ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶች የተፈራረሙ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የቴክኒክ፣ ኢኮኖሚክና ሳይንሳዊ ትብብራቸውን ለማጎልበት የተፈራረሙት ስምምነት ይጠቀሳል።