ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ የሃይማኖት መቻቻልንና ሰላምን ጨምሮ በጋራ ፍላጎቶች በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ያላትን ቦታ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሐረር ከተማ፣የአል ነጃሺ መስጂድ እና የሶፍ ዑመር ዋሻ በተባበሩት መንግስታት የባህል፣ሳይንስና ትምህርት ተቋም(ዩኔስኮ) የተመዘገቡ እስላማዊ ቅርሶችን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊ መስጂዶችና ሰነዶች ባለቤት ናት ብለዋል።
የዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ሙሐመድ ቢን አብዱልከሪም አል-ዒሳ የኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር የረጅም ጊዜ ታሪክን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከቋሬሾች ጭቆና ሸሽተው ለመጡ ሙስሊሞች መጠለያ በመስጠት የፈጸመችው ተግባር ታሪክ የማይረሳው መሆኑን አመልክተዋል።