ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀ ነው--የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ ገለጹ።

19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ የሚኒስትሮች መደበኛ ጉባዔ "የአፍሪካን የአካባቢ ችግሮች ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም፤ ትብብርን ማጎልበት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ከ51 የአፍሪካ አባል አገራት የተውጣጡ የአካባቢ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአካባቢ ጥበቃ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ባለው ችግር ሳቢያ የበረሃማነት መስፋፋት፣ የድርቅ እና የጎርፍ አደጋ የአህጉሪቱ ፈተና መሆኑ ተነስቷል።

በመሆኑም አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ላስቀመጠችው ግብ መሳካት የበለጸጉ አገራት የገቡትን ቃል መፈፀም አለባቸው ተብሏል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሳንዶካን ደበበ፤ ኢትዮጵያ ዜጎቿን በማሳተፍ ቀጣይነት ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ-ግብር እያከናወነች መሆኑን አብራርተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ-ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመከላከልና የአካባቢ መራቆትን ከመቀነስ ባለፈ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ዓላማ በመሰነቅ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘላቂና የማያቋርጥ ልማት እየተገበረች መሆኑን አስረድተዋል።

ከግብርና እና የአረንጓዴ ልማት በተጨማሪ በታዳሽ የኃይል ልማትም ለአካባቢ ደኅንነት ተስማሚ የልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው፤ ጉባዔው የአፍሪካ ሚኒስትሮች በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን አካባቢያዊ ስምምነቶች ላይ ወጥ አህጉራዊ አቋም እንዲይዙ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣዩ መስከረም ወር በሚካሄዱት አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኬሚካል አወጋገድ ጉባዔዎች ላይ ለሚቀርቡ ሃሳቦችም ግብዓት የሚሰበሰብበት ይሆናል ብለዋል።

ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚካሄደው መደበኛ ጉባዔ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በመገምገም የቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡበት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም