ሰላማችንን ጠብቀን ልማታችንን እናስቀጥላለን - የደሴ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላማችንን ጠብቀን ልማታችንን እናስቀጥላለን - የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ ፤ ነሐሴ 8/2015(ኢዜአ)፡- የአካባቢያቸውን ሰላም ጠብቀው የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በደሴ ከተማ ተወያይተዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ መሃመድ አሚን ኑርዬ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማው የልማት ጥያቄያች መልስ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ በልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ሰሞኑን በነበረው የሰላም እጦት የልማት ስራዎች በመቋረጣቸው ማዘናቸውን ጠቁመው ፤ ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የልማት ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከመንግስት ጎን ተሰልፈን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ያለሰላም ወጥቶ መግባትም ሆነ ልማት ማስቀጠል የማይቻል በመሆኑ የአካባቢያቸውን ሰላም በጋራ እንደሚጠብቁ የተናገሩት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሉባባ ሁሴን ናቸው፡፡
"ባለፈው ጦርነት ከደረሰብን ጉዳት ሳናገግም ሌላ ጦርነት አንፍልግም፣ ሰልችቶናል ያሉት ወይዘሮ ሉባባ፤ ችግሮች ሲከሰቱ በውይይትና በንግግር መፍታት አለብን" ብለዋል፡፡
የተጀመሩ ልማቶች እንዲቀጥሉና እንዳይደናቀፉ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"የችግሮች መፍቻ አኩሪ ባህልና እሴቶቻችንን ጠብቀን፣ እርስ በእርስ ተደጋግፈንና ተጋግዘን አንድነታችንን ማስቀጠል አለብን" ያሉት ደግሞ አቶ መስፍን አሸናፊ ናቸው፡፡
ሰላምን በመጠበቅ የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
ከመንግስትና ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው ሰላምንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረትም የድረሻቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ የሀገር መከታ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን ስም በማጠልሸትና ሰላምን በማወክ ልማትን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን በጋራ መታገል አለብን ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በተከሰተው ችግር በከፍተኛ ወጪ እየተሰሩ ያሉ የልማት ተግባራትን መስተጓጎላቸውን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ ልማቱን እንዲያስቀጥል አሳስበዋል፡፡
በከተማው ያለውን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል የኑሮ ውድነቱን፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በደሴ ከተማ ሁሉም የመንግስትና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍት ሆነው ህብረተሰቡን እያገለገሉ መሆናቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል፡፡
የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጋራ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከውጭ ጠላት ይጠብቃል እንጅ በየሰፈሩ የሚፈጠሩ ችግር በመፍታት መጠመድም ሆነ ጊዜውን ማጥፋት የለበትም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም እንደየአካባቢያቸው ባህልና እሴት ችግሮችን እየፈቱ የኢትዮጵያን እድገትና ልማት ማፋጠን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የጸጥታ ችግርም በውይይት ጭምር እንዲፈታ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ልማቱን ለማስቀጠል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡