ሁሉም ባለው አቅም በመረዳዳት የወገኖቻችን ችግር እንዲቀረፍ ማገዝ ይገባል-ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ - - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ባለው አቅም በመረዳዳት የወገኖቻችን ችግር እንዲቀረፍ ማገዝ ይገባል-ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ -
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ)፡- ሁሉም ባለው አቅም በመረዳዳት የወገኖቻችን ችግር እንዲቀረፍ ማገዝ ይገባል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ ገለጹ
የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራን አስጀምረዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ፤ በወረዳው የአሥር አቅመ ደካሞች ቤት እድሳት አስጀምረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 300 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም አበርክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ''ሁሉም ባለው አቅም በመረዳዳት ወገኖቻችንን ከጊዜያዊ ችግር ማላቀቅ ይኖርብናል” ብለዋል።
የነገ ትውልድ ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገናል ሲሉም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
''በአንድነት ስንተባበር የማንፈታው ችግር የለም'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይህን የአብሮነት ባህላችንን ማጠናከር አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን የመተባበር እሴታችን የማንነታችን መገለጫ በመሆኑ ይኸው እንዳይጠፋ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
የቤት እድሳት ከተጀመረላቸው አቅመ ደካሞች መካከል ወይዘሮ እርገዱ ጉርሙ እንዳሉት፤ ድጋፉ ከዚህ በፊት ከነበረባቸው ችግር እንደሚያወጣቸው ተስፋ አድርገዋል።
ለተደረገላቸው ድጋፍ በማመስገን ለቀጣይ ህይወታቸው ትልቅ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችም የተደረገላቸው ድጋፍ በትምህርታቸው የበለጠ ጠንክረው እንዲማሩ እንደሚያበረታታቸው ተናግረዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ መስቀላ በበኩላቸው፤ በወረዳው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዚህ ዓመት 24 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንደሚከናወንና የ140 የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት እንደሚካሄድ ጨምረው ገልፀዋል።
ከድጋፉ በተጨማሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች አረንጓዴ አሻራቸውንም አኑረዋል።