ቀጥታ፡

ዩኒሴፍ በጋምቤላ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያደረገ ባለው ድጋፍ ውጤቶች ተገኝተዋል - ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015(ኢዜአ)፡-የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በጋምቤላ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያደረገ ባለው ድጋፍ “በርካታ ውጤቶች” እንደተመዘገቡበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ድርጅቱ በክልሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አድማስ እንዲያሰፋም ጠይቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በክልሉ በመከናወን ላይ ባሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ላይ ከዩኒሴፍ ተወካዮች ጋር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።

አቶ ኡሞድ ድርጅቱ በክልሉ በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሌሎችም ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ በክልሉ በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍና በሌሎችም ዘርፎች በተጀመሩት ስራዎች ላይ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

መንግስት በተለይም የሕጻናትን ደህንነት ለማስጠበቅና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ለመረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም በትምህርትና በጤና ተቋማት ተደራሽነት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሌሎችም ዘርፎች የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ዶክተር አቡበከር የገለጹት።

ዩኒሴፍ የተጠቀሱት ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑና ሕብረተሰቡ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተል።

በተጨማሪም ድርጅቱ የክልሉ መንግስት ለጀመራቸው ስራዎች መጠናከር በትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም