ሠራዊቱ የአገርን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶችን እያከናወነ ነው--ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ የአገርን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶችን እያከናወነ ነው--ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ
ሐረር ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ) ፦ ሠራዊቱ የአገርን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ ተናገሩ።
ዕዙ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ በ320 ሄክታር መሬት ላይ የግብርና ልማት ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል።
ሠራዊቱ በሚያከናውናቸው የስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች ከራሱ ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተመላክቷል።
ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ እና ግዳጅ በብቃት ከመወጣት ባሻገር በልማት ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
መንግስት በመኸር ወቅት ሳይታረስ የሚቀር መሬት መኖር እንደሌለበት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መከላከያ ሠራዊቱም በተለያዩ አካባቢዎች ሳይታረሱ የሚያድሩ መሬቶች መልማት አለባቸው በሚል የግብርና ልማት ሥራውን መጀመሩን ተናግረዋል።
በልማቱ ሠራዊቱ በግብዓት የአካባቢው ማህበረሰብ ደግሞ በግብዓትና በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን መታቀዱንም ሌተናል ጀነራል መሀመድ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ በምስራቅ ቀጠና የልማት ስራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የሚያከናውነውን የልማት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ለልማቱ ስኬታማነት ከዕዙ ጎን በመሆን ድጋፍ ላደረጉ የምስራቅ ሐረርጌ ዞንና የባቢሌ ወረዳ አስተዳደር እንዲሁም ሙያዊ እገዛ እያደረገ ላለው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጀነራል መኮንኑ ምስጋና አቅርበዋል።
ዕዙ በምስራቅ ቀጠና 320 ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ዕዝ ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ሐሰን ሰኢድ ናቸው።
በምስራቅ ቀጠና ሦስት ቦታዎች ላይ በሚከናወነው የልማት ሥራም ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በልማት ሥራው ለወጣቶችና ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል መከፈቱን የጠቀሱት ኮሎኔል ሀሰን፣ በቀጣይም በከብት እርባታና በሌሎች ሥራዎች የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማጠናከር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
"ዕዙ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን በግብርና ልማት መሳተፉ የአካባቢው ህዝብና አስተዳደር ይደግፈዋል" ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ ናቸው።
በተለይ መሬቱ ለበርካታ ዓመታት ሳይታረስ መቆየቱን አስታውሰው፣ መከላከያ ሠራዊት የግብርና ልማት ማከናወኑ የአካባቢው ማህበረሰብ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲቀስምና ከምርቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት በዞኑ የጀመረው የግብርና ስራ ውጤታማ እንዲሆን አስተዳደሩ በተለያዩ መስኮች እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የባቢሌ ወረዳ ኢፋአዲ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወጣት መሀመድ ተማም በበኩሉ መከላከያ ሠራዊቱ በአካባቢው የግብርና ሥራ በመጀመሩ መደሰቱን ተናግሯል።
በሠራዊቱ የልማት እንቅስቃሴ በተለይ ለወጣቱ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እንዳሉ ገልጾ፣ በቀጣይ ከሠራዊቱ ጋር በመሆን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግሯል።
"በሀገር መከላከያ ሠራዊቱ እየለማ ያለው መሬት ለዘመናት አልታረሰም፤ በአረምም የተሞላ ነበር" ያለው ደግሞ በባቢሌ ወረዳ የኤረር ኩታ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወጣት መሀመድ ጃፈር ነው።
የአገር መከላከያ ሠራዊት መሬቱን ተረክቦ ማልማት መጀመሩ ትልቅ ተስፋ ሰጥቶናል፤ በቀጣይም ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን ብሏል።