በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የዝናብ መጠን ለመኸር ሰብሎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የዝናብ መጠን ለመኸር ሰብሎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ) ፡- በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች እድገት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በቀጣዩቹ አሥር ቀናት የመኸር ሰብል አምራች በሆኑትም ሆነ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ቀጣይነት ያለው የእርጥበት ሥርጭት ሊኖር እንደሚችል ትንበያው አስታውቋል።
ይህም እርጥበት በተለያዩ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
በተለይ የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻሉ በተጨማሪ በአንዳንድ እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን ለማሰባሰብ እገዛ እንደሚያደርግ መግለጫው አመልክቷል።
በአንዳንድ የምስራቅና የደቡባዊ ክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በመጠን ዝቅተኛ የሆነ እርጥበት የሚጠበቅ በመሆኑ በእነዚህ ቦታዎች የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲልም አብራርቷል።
በሌላ በኩል ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው የሰሜንና የምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በማሳ ላይ ውሃ እንዳይተኛ ከወዲሁ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ከእርጥበት መብዛት የተነሳ የአረም መስፋፋትም ሆነ ለሰብል በሽታዎችና ተባዮች መከሰት ምቹ ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል አርሶ አደሩ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ትንበያው አመልክቷል።
በአጠቃላይ የዝናብ መጠን ከፍተኛ በሆኑ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጎርፍ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አስገንዝቧል፡፡