ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለዘላቂ የውሃ ጥበቃ ካለው ፋይዳ አኳያ ሀገራት በአርዓያነት ሊወስዱት ይገባል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለዘላቂ የውሃ ጥበቃ ካለው ፋይዳ አኳያ ሀገራት በአርዓያነት ወስደው ሊተገብሩት እንደሚገባ የውሃና ኢንርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለፁ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመልከ ብዙ ቀውሶች እየተዳረገ ላለው የአፍሪካ ቀንድ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ባለሙያዎች ያነሳሉ።

መርሐ ግብሩ በደን ሽፋንና የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃ መጨመር እንዲሁም ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ አይነተኛ ሚና እንዳለውም ይጠቀሳል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለዘላቂ ውሃ ሀብት ጥበቃ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

የሚተከሉ ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ፋይዳቸው ባሻገር ምንጮች እንዲጎለብቱ እና ለወንዞች ፍሰት መጨመር ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህም ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ መርሐ ግብሩ ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና ለውሃ ሀብት ጥበቃ ካለው ሁነኛ ፋይዳ አኳያ ሌሎች ሀገራት በአርዓያት ሊወስዱት እና ሊተገብሩት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ከሌሎች ምርምር ተቋማት ጋር በመተባበር የውሃ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 25 ቢሊዮን ችግኝ መትከሏ ይታወቃል።

በሁለተኛው ምዕራፍም 25 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በዘንድሮው ክረምት ከ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ባሻገር የማህበረሰብ አቀፍ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን ማከናወን ከጀመረች በርካታ ዓመታትን አስቆጥራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም