በአገር መከላከያ ሰራዊትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት በጎንደር ከተማ ሰላም በመፈጠሩ የአገልግሎትና ንግድ ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል--የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ - ኢዜአ አማርኛ
በአገር መከላከያ ሰራዊትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት በጎንደር ከተማ ሰላም በመፈጠሩ የአገልግሎትና ንግድ ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል--የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 (ኢዜአ) ፡- በአገር መከላከያ ሰራዊትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት በጎንደር ከተማ ሰላም በመፈጠሩ የአገልግሎትና ንግድ ተቋማት መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የከተማው ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ባዩህ አቡሀይ ገለጹ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የከተማው ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ባዩህ አቡሀይ፤ አሁን ላይ ነገሮች ሁሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል ብለዋል።
በመከላከያ ሰራዊቱ ጥበብ የተሞላበት የሕግ ማስከበር ሂደት እንዲሁም በነዋሪዎች ጥረት ችግሩ ተፈትቶ በጎንደር መደበኛ አገልግሎቶች መሰጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከያ ሠራዊት እና የከተማው የጸጥታ ኃይል በጋራ የሕግ ማስከበር ሥራውን ማከናወናቸውን አስታውሰው፤ የሕዝቡ ትብብር ታክሎበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት መቻሉን አብራርተዋል።
በቅርሶችና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተደርጎ በአንዳንድ አካላት የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልፀዋል።
በከተማዋ የግጭትና አለመረጋጋት ዓላማ ሰንቀው የነበሩ ጠላቶች አስበውት ከነበረው የጥፋት ዕቅድ አንጻር የከፋ ጉዳት አለመድረሱንም ተናግረዋል።
በመሆኑም በመከላከያ ሠራዊቱ እና በሕዝቡ ትብብር ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷንና ተቋማትም መደበኛ አገልግሎት መጀመራቸውን ገልፀዋል።
በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የንግድ እንቅስቃሴና ሌሎችም መደበኛ አገልግሎቶች ተጀምረዋል ነው ያሉት።
የግጭት፣ የጥፋትና ውድመት አማራጭ ለማንም የማይጠቅም መሆኑን የጠቀሱት የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ የሰላሙን ሂደት ማጽናት የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በየትኛውም መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በንግግር መፍታት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ጠቁመው፤ ማንኛውም አካል ነፍጡን አስቀምጦ ለውይይት የሚመጣ ከሆነ የከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሀገር መከታና የሕዝብ አለኝታ የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዋጋ ከፍሎ አገርን አቁሟል ያሉት ከንቲባው፤ መልካም የሆነ ስሙን ለማጠልሸት የሚደረግ ጥረት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልፀዋል።
ሕዝቡም የጠላቶችን አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ እንዲመክት ጠይቀው፤ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከሠራዊቱ ጎን በመቆም የሰላም አጋርነቱን እንዲቀጥል አሳስበዋል።