ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአምበጣ መንጋ ለመከላከል ግብረ-ሀይል ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል--አቶ ጌታቸው ረዳ

መቀሌ ፤ ነሐሴ 7/2015 (ኢዜአ) ፦ በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአምበጣ መንጋ ለመከላከል በክልል ደረጃ ግብረ-ሀይል ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ አስታወቁ።

ህብረተሰቡ በሰብልና ደን ላይ የተከሰተውን የአምበጣ መንጋ በመከላከል ሂደት ተሷትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የአምበጣ መንጋ ተከስቷል።

መንጋው አሁን ላይ በመኸር ሰብልና በደኖች ላይ በመስፈር ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አመልክተው ህብረተሰቡ በየአካባቢው በባህላዊ ዘዴ መንጋውን እየተከላከለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአምበጣ መንጋው ከአቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ በክልል ደረጃ ግብረ-ሀይል ተቋቁሞ የመከላከል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የአምበጣ መንጋውን ከምንጩ መከላከል የሚያስችል የኬሚካልና የአውሮፕላን ድጋፍ ከፌዴራል መንግስት እንዲደረግ ስራዎች መጀመራቸውን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም