ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ይሰራል- ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ

ሰመራ ፤ ነሐሴ 7/2015 (ኢዜአ) ፦ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ይሰራል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ አስታወቁ።

የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መርሐ-ግብር ዛሬ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት ተደራጅተንና ተቀናጅተን ከሠራን የማናሳካው ነገር የለም።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ለዘርፉ ስኬታማነት የዘርፍ ማህበራትን ማጠናከር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታትና መሰል ስራዎችን በቁርጠኝነት እንደሚያከናውን አመልክተዋል።

“ባለሃብቶች ተቀናጅተው ወደ ክልላችን በመግባት በልማት የመሰማራት ተሳትፏቸው አበረታች ነበር“ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተሳትፏቸውን በላቀ ሁኔታ ለማስቀጠል ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ጠቁመዋል።

ለተግባራዊነቱም ከፌዴራል መንግስት ጋር በጋራ በማቀድ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው “በዘርፉ ዘላቂ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው አምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መሪነቱን ድርሻ ሲረከብ ብቻ ነው” ብለዋል።

“ዘርፉ የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚ በላቀ ደረጃ ማበርከት ካልቻለ ኢኮኖሚያችን ዘላቂ ተወዳዳሪ ሊሆን አይቻለውም” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለተግባራዊነቱ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኘሮጀክት ጽህፈት ቤት ኀላፊ አቶ አስፋው አበበ በንቅናቄ መድረኩ ላይ ባቀረቡት ፅሁፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዋና ዓላማ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆ በተቀናጀ አግባብ መፍታትና ምቹ የቢዝነስ ከባቢ መፍጠር መሆኑን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ የዘርፉን ሽግግር ለማፋጠን ማዕከል አድርጎ የተቋቋመ መሆኑን በማከል።

በንቅናቄው ተቋማዊ ዘለቄታን በመፍጠር አንድ የጋራ መግባባት በማስቀመጥ በአገር ውስጥ ምርት የሚኮራ ትውልድ መፍጠር እንደሚያሻ አስገንዝበዋል።

በአፋር ክልል 169 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የዕቅድ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል አባተ ናቸው።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተሳተፋ ባለሃብቶች በዘርፉ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማንሳት መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ጠይቀዋል።

የንቅናቄ መድረኩን ተከትሎ በሠመራ ከተማ የሚገኙ ፋብሪካዎች የተጎበኙ ሲሆን የምርት ትውውቅም ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም