የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ በትኬት ሽያጭ ያስገባውን ገቢ በውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ እየሰራ ነው - መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ በትኬት ሽያጭ ያስገባውን ገቢ በውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ እየሰራ ነው - መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ በትኬት ሽያጭ ያስገባውን በዶላር፣ በፓውንድና በዩሮ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዶች በገቡት ውል መሰረት የቲኬት ሽያጭ በአገራት የመገበያያ ገንዘብ ይፈጸማል።
ይህንንም ተክትሎ በአገራት የመገበያያ ገንዘብ በሚካሄድ የቲኬት ሽያጭ የተገኘውን ገቢ ለቲኬቱ ባለቤት አየር መንገድ በዶላር፣ በፓውንድ ወይም በዩሮ ተቀይሮ ገቢ እንደሚደረግለት አንስተዋል።
በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ አገራት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም አየር መንገዱ በተለያዩ አገራት የመገበያያ ገንዘብ ያስገባውን ገቢ በወቅቱ እየሰበሰበ መሆኑን ገልጸው በአፍሪካ አገራት ግን አየር መንገዱ ያስገባውን ገቢ በዶላርና በዩሮ ቀይሮ በማስረከብ ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ነው ያነሱት።
በዚህም አየር መንገዱ በተለያዩ አፍሪካ አገራት አየር መንገዶች ከትኬት ሽያጭ ያገኘው ከ180 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ እስካሁን ሳይከፈለው መቆየቱን አየር መንገዱ ገልጿል።
ይህንንም ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀመጫውን ካናዳ ካደረገው ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይአታ) ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይአታ) ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገባውን ገቢ በዶላርና በዩሮ በሚቀበልበት ምቹ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያነሱት።
ጎን ለጎንም አየር መንገዱም ከተለያዩ የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ከአገራት የኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚተሳሰር መሆኑን ጠቅሰው በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህን ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ አገራት በተለይም ምጣኔ ኃብታዊ እድገታቸውን አጠናክሮ ማስቀጠልና የውጭ ምንዛሬ ግኝታቸውን በዛው ልክ ማጎልበት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ በአፍሪካ በጅምር ደረጃ ላይ ያለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናም የአፍሪካን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት እውን ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ 134 ዓለም አቀፍ መደራሻዎች ያሉት ሲሆን በቅርቡም በአውሮፓና በአፍሪካ ስድስት አዳዲስ መዳረሻዎቹን ለመጨመር እየሰራ መሆኑን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።