ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ መካሄድ ጀመረ

ሰመራ ፤ ነሐሴ 7/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሠን መሐመድ እና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኘሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስፋው አበበ ለዚሁ ዓላማ ሰመራ ከተማ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እና የኢትዮጵያ ኢንተርኘራይዝ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌዴራል የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው።

በአፋር ክልል የንግድ ገበያ ልማት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አዘጋጅነት የተዘጋጀው የንቅናቄ መድረኩ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የሚያሳድግ እንደሆነም ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በጋራ መፍታት የሚያስችልና ለዘርፉ ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሚያስችል እንዲሁም ለኢኮኖሚ ሽግግር አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።

በንቅናቄ መድረኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ኢንዱስትሪዎቹን የሚደግፉ አካላት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል።

የንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊዎች ሰመራ ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እንደሚጎበኙና የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም