በአዳማ ዙሪያ የሚገኙ  26  የገጠር ቀበሌዎችና ሁለት የከተሞች  አስተዳድሮች ወደ አዳማ ከተማ አስተዳደር ተጠቃለሉ

አዳማ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ)፡- የአዳማ ከተማን በዙሪያው ካሉ ቀበሌዎች ጋር በመሰረተ ልማት አስተሳስሮ የጋራ ልማትና ዕድገትን ለማረጋገጥ እንዲቻል 26 የገጠር ቀበሌዎችና የሁለት ከተሞች አስተዳድሮች ወደ አዳማ ከተማ አስተዳደር ተጠቃለሉ።

የአዳማ ከተማ እና የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደሮች በአዳማ ከተማ አስተዳደር ስር የተጠቃለሉ የሁለቱን ከተሞች  አስተዳድሮችና  የ26 የገጠር ቀበሌዎችን  ርክክብ ዛሬ አካሂደዋል።


 

በአዳማ ከተማ አስተዳደር የተቀላቀሉትን የወንጂና የአዋሽ መልካሳ ከተሞች አስተዳድሮችን እና የገጠር ቀበሌዎቹን በልማት ለማስተሳሰር ወሳኝ መሆናቸውን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል።

በተለይ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች በዙሪያዋ ካሉት ቀበሌዎች አርሶ አደሮች ጋር የጋራ ልማትና እድገት እንዲኖራቸው ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

የከተማዋ ህብረተሰብ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ያሉበትን የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የራሱ አስተዋጾ እንደሚኖረውም ከንቲባው ጠቁመዋል። 


 

የከተማ አስተዳደሮቹና የገጠር ቀበሌዎቹ ወደ አዳማ ከተማ አስተዳደር መቀላቀል ህብረተሰቡና አርሶ አደሮችን ያቀፈ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ወሳኝ መሆኑን ከንቲባው  ተናግረዋል።

እንዲሁም የአዳማ ከተማን የንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና የኮንፍረንስ ማዕከልነቷን ይበልጥ ለማረጋገጥ ያለመ ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል።

ከንቲባ ኃይሉ እንዳሉት የማካለሉ ስራ በየአቅጣጫው እየሰፋች ያለችውን የአዳማ ከተማ ዕድገት ደረጃውን በጠበቀ ማስተር ፕላንና የልማት ዕቅድ ለመምራት የሚያግዝ ነው።

በተጨማሪም የመሬት ሀብትን በአግባቡ ለማስተዳደርና የአጠቃቀም ሥርዓት ለማዘመን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ "ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመቆጣጠርና ለማስቆምም ያስችላል" ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት 13 ሺህ ሄክታር መሬት ስፋት ያላት ሲሆን፤ አሁን ወደ አዳማ ከተማ አስተዳደር የተቀላቀሉት ሁለት የከተማ አስተዳደሮች እና 26 የገጠር ቀበሌዎች የከተማዋን የቆዳ ስፋት በሦስት እጥፍ እንደሚያሳድገው አመላክተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው  ወደ አዳማ ከተማ የገቡት ቀበሌዎች ቀደም ሲል በሉሜ፣ ቦሰት እና አዳማ ወረዳዎች ሥር የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀበሌዎቹ ሲካለሉ ከ40 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ  ወደ አዳማ ከተማ መግባቱን ጠቁመው፣ "ይህም የአርሶ አደሩንና የከተማዋን ነዋሪ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው" ብለዋል።

የከተማ ግብርና ኢንሼቲቭ፣ የእንስሳት ሀብት፣ የአትክትልና ፍራፍሬ ልማትን ለማስፋፋት እንዲሁም ለአምራቹ አርሶ አደር ተገቢውን ድጋፍ፣ የገበያ ትስስርና መሰረተ ልማትን ለማቅረብ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቆምና ሀብቱን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያግዝ መሆኑንም አቶ አባቡ አመልክተዋል።

የማካለሉን የአፈጻም ሂደት በማስመልከት ሪፖርት ያቀረቡት የአካላይ ኮሚቴው ተወካይ አቶ ስዩም አጥሌ በማካለል ሂደት በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ከ7 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን አስረድተዋል።

በእዚህም ቀበሌዎቹ ወደ አዳማ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ በመደረጉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና የጋራ ልማትና ዕድገት እንደሚያረጋግጥ በጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

ወደ አዳማ አስተዳደር የተካለሉ ቀበሌዎች ውስጥ የሚሰሩ የጤና ኤክስቴንሽንና የግብርና ልማት ባለሙያዎች፣ መምህራን እንዲሁም ሌሎች የአስተዳደር ሠራተኞች በሙሉ ከወረዳዎቹ ወደ ከተማዋ መጠቃለላቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪ አርሶ አደሩ ለሚያመርተው ምርት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲያገኝ ከማስቻል ባሻገር የልፋቱ ውጤት ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።

የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብአቶችንና የገበያ አማራጮችን በቅርበት እንዲያገኝ እንደሚያስችለው በጥናት ተለይቶና ታምኖበት ዛሬ ርክክብ ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም