የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና አገሩን በጀግንነት የሚያገለግል ሰራዊት ተገንብቷል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና አገሩን በጀግንነት የሚያገለግል ሰራዊት ተገንብቷል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና አገሩን በጀግንነት የሚያገለገል የሀገር መከላከያ ሰራዊት መገንባቱን የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
የኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ እዝ ያሰለጠናቸውን 41ኛ ዙር ዞብል ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶዎችንና ልዩ ሃይል ጸረ ሽብር አባላት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት አስመርቋል።
የኮማንዶና ልዩ ሃይል አባላቱ ፈታኝ የሆነውን ስልጠና በስኬት በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመጥንና አገሩን በጀግንነት የሚያገለግል የሀገር መከላከያ ሰራዊት መገንባቱን ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጀግንነት መስዋትነት በመክፈል ኢትዮጵያ እንድትጸና አኩሪ ገድል እየፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬዎቹ የአየር ወለድና የኮማንዶ ሰራዊት ዋነኛ ዓላማ ውጊያን አስቀድሞ የሚያስቀር፣ አልፎ ከመጣ ደግሞ በአጭር ጊዜ በድል ማጠናቀቅ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቀዳሚ ፍላጎት ሰላም መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ አኩሪ ስራ ማከናወኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልእኮ በብቃት መወጣት የሚችል ሰራዊት መገንባቷንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችም ከምንም በላይ አገራቸውንና ህዝባቸውን በማስቀደም የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም ዘወትር ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል።