ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፣ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በመላበስ የአገሩ መከታ በመሆን በጠንካራ ቁመና ላይ ይገኛል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ)፡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በመላበስ የአገሩ መከታ በመሆን በጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ እዝ ያሰለጠናቸውን 41ኛ ዙር ዞብል ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶዎችንና ልዩ ሃይል ጸረ ሽብር አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት አስመርቋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ ዘመናዊ የጦር ሃይል ተገንብቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከየትኛውም የጥፋት ሃይል የሚታደግ ጠንካራና ዘመናዊ ሰራዊት መገንባቱንም ነው የተናገሩት።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በመላበስ የአገሩ መከታ በመሆን በጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ መሆኑን በተግባር ማሳየቱንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይም የሰራዊቱ ግንባታ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም