ቀጥታ፡

በጋራ የተገነቡ መልካም እሴቶችን በማጠናከር በህዝቦች መካከል ያለውን ጤናማ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት መስራት ይገባል

ሀዋሳ ነሀሴ 6/2015(ኢዜአ).፡-በጋራ የተገነቡ መልካም እሴቶችን በማጠናከር በህዝቦች መካከል አንዱ ለሌላው የሠላምና የልማት ኃይል እንዲሆን ጤናማ ግንኙነቶችን በበለጠ ለማጎልበት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ገለጹ።

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት  የመጨረሻውን አስቸኳይ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።


 

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በህዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች መሠረት የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአሁኑ ወቅት በአራት ክልሎች መደራጀቱን ገልጸው፤ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የዳበሩ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቅሰዋል።

ዋና አፈ ጉባኤው አያይዘውም እነዚህ በጋራ የተገነቡ መልካም እሴቶችን በማጠናከር በህዝቦች መካከል አንዱ ለሌላው የሠላምና ልማት ኃይል እንዲሆን የሚያደርጉ ጤናማ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲዳብሩ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ ከተመሰረተበት ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ተልዕኮውንና ኃላፊነቱን ለመወጣት በክልሉ የሚኖሩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸው፣ ባህልና እሴቶቻቸው እንዲታወቁና እንዲጉለብቱ ውጤታማ ሥራዎችን እንዳከናወነም ዋና አፈ ጉባኤው ገልፀዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ የነበሩ የማንነት፣ የወሰንና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

ግጭቶችን በሰከነ መንገድ መፍታት የሚያስችል የግጭት አፈታት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ በህዝቦች መካከል ያለው አብሮነትና ትስስር በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሰራቱንም ጠቁመዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ የማጎልበት ስራ መስራቱን ተናግረዋል።


 

ከዚህ ባለፈ የጋራ እሴቶቻችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በህዝቦች መካከል ወንድማማችነት እንዲዳብር በማድረግ ረገድም ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በማንነቶች ውስጥ ያለው ብዝሀነት እንደተጠበቀ የክልሉ ህዝቦች አንድነታቸው እንዲጠናከር ምክር ቤቱ ያበረከተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በህዝቦች መካከል ያለው መስተጋብር በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመራ በማድረግም ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ጉልህ ሚና መጫወቱን ኃላፊው  ገልፀዋል፡፡

አቶ ጥላሁን አያይዘውም "እስከ አሁን የገነባነው ወንድማማችነትና ቤተሰባዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲዳብርም መስራት አለብን" ብለዋል፡፡    

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ሻምበል ሻኜ "ምክር ቤቱ ባለፉት 20 ዓመታት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እርስ በርስ በማስተዋወቅና በማስተሳሰር ትልቅ ድርሻ ነበረው" ብለዋል፡፡

በአደረጃጀት ብንለያይም አንድ የሚያደርጉን በርካታ እሴቶች አሉን ያሉት አቶ ሻምበል እነዚህን ይበልጥ የማዳበርና የነበረው አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ የማድረግ ሥራ መሰራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሕዝቦችን እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ እሴቶች በማጉላት በልማትም ሆነ በሌሎች መስተጋብሮች በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በቅንነት በመወጣትም ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉም መክረዋል፡፡

በጉባኤው ላይ ለምክር ቤቱ አባላት የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም