ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ኮማንደሮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን የለውጥ ሥራዎች ጎበኙ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ)፡-የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ኮማንደሮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የለውጥ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የፖሊስ ፐርሶኔል ኮሎኔል ቴራንስ ባሁፍሰ ከዘጠኝ አባል ሀገራት የተውጣጡ የፖሊስ ኮማንደሮችን በፖሊሳዊ ስልጠና ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ባካበተው በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናዎችን እየወሰዱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን አስቀድሞ በጋራ ለመከላከል እንዲቻል የፖሊስ ኮማንደሮችን ዝግጁ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም 24 ሰዓት ወንጀልንና የትራፊክ አደጋን ለመቆጣጠር እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመመልከታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።


 

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አሰልጣኝ ሱፔር ኢንተንደንት ዋኒያማ ሞሴስ በበኩላቸው ስልጠናው በሲቪሎች ደህንነትና ጥበቃ፣ በተጠባባቂ ኃይሉ ተልዕኮ ሰራተኞች እና መገልገያ ግብዓቶች ጥበቃ እንዲሁም በመንግስት የልማት እርዳታ አስተዳደር ላይ የሚሰሩ የፎርሚድ ፖሊስ ዩኒት (FPU) ኮማንደሮችን ለስታንድ ባይ እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሰልጣኝ አስፒ ሞኒካ ካራንጃ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የከተማዋን ደህንነትና የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀው፤ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል አባል ሀገራት ይህንን ልምድና ተሞክሮ ወደ ራሳቸው ወስደው ማስፋት እንዳለባቸው ጠቁመው ተቋሙ የጀመረውን ለውጥ በያዘው ፍጥነትና ጥራት መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡


 

የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ ተግባራትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ አሰራሩን ላሻሻሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ያላቸውን አድናቆት ገልፀው ኮማንደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ለተዘጋጀላቸው ስልጠና እንዲሁም ጉብኝቱን አመቻችቶ የለውጥ ስራዎቹን እንዲመለከቱ በማድረጉ የተሰማቸውን ልባዊ ምስጋና መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም