ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሳካት የአይሲቲ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ሊያግዙ ይገባል-አቶ ንጉሡ ጥላሁን - ኢዜአ አማርኛ
ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሳካት የአይሲቲ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ሊያግዙ ይገባል-አቶ ንጉሡ ጥላሁን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ)፡-ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሳካት በአይሲቲ ዘርፍ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች ሊያግዙ እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለአራት ወራት ሲካሄድ የቆየው የብሩህ አይ ሲ ቲ የንግድ ስራ የፈጠራ ሀሳብ ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።
በውድድሩና በነበሩ ስልጠናዎች 77 ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያቃልሉ እና አገልግሎቶችን የሚያዘምኑ 51 የዲጂታል የንግድ የፈጠራ ሀሳቦች ቀርበዋል።
በአጠቃላይ በተካሄዱ ውድድሮች ምርጥ የፈጠራ ሀሳብ በማቅረብ ላሸነፉ 10 ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው የ260 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በ2015 በጀት ዓመት የስራ እድል ፈጠራ ማስፋፋት ላይና በቂ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።
የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች የሀገሪቱን ልማት የሚያፋጥኑና ሀገራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልፀው ይህንንም ለማድረግ ሚኒስቴሩ ዘላቂነት ያላቸውን የስራ ዕድሎች ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም፤ መንግስት የስራ እድል ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች የሚያበረታቱ መርሐ ግብሮችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ስራ እና ሀሳብ ወደ ገበያ የሚያቀርቡባቸው ዕድሎች እየተመቻቹ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለአብነትም በአይሲቲ ዘርፍ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶችን በማወዳደር እና ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ ስራዎቻቸውን ለማስፋፋት የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳካት ባለሀብቶች በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ የፈጠራ ሀሳብ ባለቤት ወጣቶችን በመደገፍ ሚናቸውን እንዲወጡም ነው አቶ ንጉሡ የጠየቁት።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የፈጠራ ሀሳቦች ማበልጸጊያ ዴስክ ሃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ደርሶልኝ በበኩላቸው፤ የውድድር ተሳታፊ ወጣቶች የንግድ የፈጠራ ሀሳብ አቀራረብን ጨምሮ የአቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ወጣቶቹ በግብርናው ዘርፍ፣ በአገልግሎት፣ በትምህርት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተሻለ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ጠቁመዋል።
የውድድሩ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ለሀገራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የሚያመጡ የፈጠራ ስራዎች ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦቻቸው አሸንፈው መሸለማቸው ይበልጥ ለመስራትእንዳነሳሳቸውም ነው የገለጹት።