ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል እየተካሄዱ ያሉ የበጎ አድራጎት ስራዎች  አበረታች ናቸው - የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ቀጀላ መርዳሳ

ሐረር ፤ ነሐሴ 6 / 2015 (ኢዜአ) ፡- በሐረሪ ክልል እየተካሄዱ ያሉ የበጎ አድራጎት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ  የሚበረታቱ መሆናቸውን  የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ። 

የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በሐረሪ ክልል የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፣የአረጋውያን ቤት እድሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መረሃ ግብር አካሄደዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣  ብሔረሰቦችና ህዝቦች በበጎ አድራጎት ስራዎች የታወቁ ናቸው።


 

በተለይ አብሮ የመኖር፣መተጋገዝና መደጋገፍና መረዳዳት የኢትዮጵያዊያን አኩሪ መገለጫ እሴታቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

የበጎ አድራጎት ስራዎችም  ለሰው ልጅ ያለንን ርህራሄ የምናሳይበት የተቀደሰ ተግባር ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤  በሐረሪ ክልል በተለይ ህጻናትን ከሚያጋጥማቸው የተለያዩ ችግሮች ለመታደግ እየተከናወኑ ያሉ የበጎ አድራጎት ስራዎች አበረታች መሆናቸውንና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማትም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ከማከናወን ባለፈ፤ መጽሐፍትና ደብተሮች ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በሐረሪ ክልል በተለይም  የ"ሐረር ልጅ የበጎ አድራጎት ማህበር"  እያከናወናቸው ያሉት  የበጎ አድራጎት ተግባራት የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ  ወርቅነሽ ብሩ ናቸው። 


 

ማህበሩ በከተማው ህጻናትን ከሚደርስባቸው ችግሮችን በመታደግ ለተሻለ ህይወት እንዲበቁ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ መረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ከዛሬው  በተጨማሪ  ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ሚኒስትር ዴኤታዋ  ቃል ገብተዋል።

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም በበኩላቸው፤ለአቅመ ደካማ ቤት መጠገን፣ህጻናትን መደገፍና መንከባከብ   የህሊና እረፍት የሚሰጥና የተቀደሰ ተግባር ነው ብለዋል።

በክልሉ በየዓመቱ  የበጎ አድራጎት ስራዎች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ በተለይ ዘንድሮ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና  ተጠሪ ተቋማት ያስጀመሩት የበጎ ፍቃድ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል። 

በሚኒስቴሩና  ተጠሪ ተቋማቱ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የሐረር ልጅ የበጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት ተስፋ አለባቸው ፤ ህጻናት ለተለያዩ ችግሮች እንዳይጋለጡ በማህበሩ ማቆያ ስፍራ  የማስተማርና የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።

የተደረገው ድጋፍ ህጻናቱ ከትምህርት ገበታቸው ላይ ሳያቋርጡ በአግባቡ መማር እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሶ፤  ለድጋፉ ምስጋና አቅርቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም