ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች ደም ለገሱ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ) ፡-ከ 1 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች ደም ለገሱ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች በየዓመቱ  የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ያካሂዳሉ፤ የዛሬው የደም ልገሳ መረሃ ግብርም የዚሁ አካል ስለመሆኑ ተነግሯል።

በደም ልገሳው የተሳተፉ የተቋሙ ሰራተኞች ከፍያለው በዳሳ፣ተስፋነህ እስጢፋኖስ እና የትናየት ወርቁ ለኢዜአ  እንደገለጹት ሰዎች ከሚያደርጉት በጎ ተግባራት መካከል ደም መለገስ ትልቁና ዋነኛው ነው።

የሰዎችን ህይወት በመታደግ የህሊና እርካታ  በሚሰጠው የደም ልገሳ ላይ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

''የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከህዝብ የወጣ ለህዝብ የሚያገለግል በመሆኑ አስፈላጊ በሆኑ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍና አጋርነቱን በተግባር መግለጽ ያስፈልጋልም'' ብለዋል።

ይሁን እንጂ ደም መለገስ የዘመቻ ስራ መሆን የለበትም ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የደም ፍላጎት የማይቋረጥ በመሆኑ ልገሳውም በተከታታይ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ነው  ያሉት።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አልሰን አሰፋ በበኩላቸው ባንኩ ከተቋቋመበት ዓላማ ጎን ለጎን በተለያዩ ማህበራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ነው።

በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለውን የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የስራው አካል በማድረግ የተለያዩ የበጎ ስራ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ከ1 ሺህ 200 በላይ የተቋሙ ሰራተኞች የተሳተፉበት  የደም ልገሳ መረሃ ግብር የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የደም ልገሳው  የባንኩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችም ጭምር እንደሚካሄድ ገልጸው ደም ልገሳን ባህል በማድረግ አብሮነትንና አንድነትን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም