ቀጥታ፡

በስራ እድል ፈጠራ የታዩ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል የጋራ ጥረቶች ሊደረጉ ይገባል- የስራና ክህሎት ሚኒስትር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ) ፡-  "በስራ እድል ፈጠራ የታዩ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ የጋራ ጥረቶች ሊደረጉ ይገባል" ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

በተያዘው በጀት ዓመት ለ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።      

የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን የበለጠ ለማጎልበት የሚረዳ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ  በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል። 


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በስራ እድል ፈጠራ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች አሉ ብለዋል። 

በክልሎች ያሉ ጸጋዎችን በመለየት ስራ መፍጠር፤ በተለይም በገጠር አካባቢዎች ያለውን አቅም በአግባቡ  መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በመሆኑም በስራ እድል ፈጠራ የታዩ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ የጋራ ጥረቶች ሊደረጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የግብርናው ዘርፍ ካለው አቅም አኳያ እየተፈጠረበት ያለው ስራ አነስተኛ መሆኑን የጠቀሱት በቀጣይ በዘርፉ ብዙ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የባዮ ሜትሪክስ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው  በ2015 በጀት ዓመት ለ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በግብርናው፣ በአገልግሎት እና አምራች ዘርፉ ለ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ የመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።   

ለእቅዱ ስኬት 48 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ አቅርቦት ይጠይቃል ያሉት አቶ ንጉሱ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አሁንም ማነቆ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ከዓመታዊ ብድር ምጣኔያቸው 5 በመቶ የሚሆነውን ለኢንተርፕራይዞች ማቅረብ የሚኖርባቸው ቢሆንም ድንጋጌውን ማክበር ባለመቻላቸው የብድር አቅርቦቱን ፈታኝ አድርጎታል" ነው ያሉት። 

ከዚህ ባሻገር ማይክሮ ፋይናንሶች ከማህበራዊ መሰረታቸው ውጭ ብድሮችን እያቀረቡ መሆኑን የፋይናንስ አቅርቦቱ ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ተናግረዋል። 

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የመስሪያ ቦታ ሼድን በተመለከተም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር ለክልሎችና ለከተማ መስተዳደሮች የሚቀርብበት ስርዓት መዘርጋቱንም በማከል። 

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የቴክኒኪና ሙያ ኮሌጅ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

   

 

 

 

      

 

 

 

  

 

 

 

 

 

  

 

 

 

 

 

     

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

   

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም