ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት፣ መስኖና የምግብ ዋስትና

በሰለሞን ተሰራ

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ እንደሚያመለክተው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ወይም 29 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠለትም።

ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ደግሞ 43 በመቶ የሚሆኑ ህዝቦች የምግብ ዋስትና እንዳልተረጋገጠላቸው የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል። 

አገራት አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋስትና ጉዳይ በተለይ እ.አ.አ. ከ1970ዎቹ ጀምሮ የመወያያ ጉዳያቸው በማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ሲያመላክቱና ሲሰሩ መቆየታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በ1990ዎቹ መጨረሻ ግን ከሚሊኒየሙ የልማት ግቦች የመጀመሪያው ከሆነው ርሀብን የማጥፋት ዘመቻ ጋር እንዲያያዝ ተደርጎ በመታሰቡ አገራት የምግብ ዋስትናን ጉዳይ የፖሊሲዎቻቸው አካል በማድረግ እየሰሩበት ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ በሚያጋጥሟት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎቿ ለችግር ይዳረጋሉ። 

በዘላቂነት ከችግር መውጫ መንገዱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መሆኑ ታምኖበትና አሰራሮች ተቀርጸው ወደ ስራ ከተገባ ውሎ አድሯል።

በተለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በግብርና ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ከሚፈጥረው ችግር ለመላቀቅ የሚያስችሉ ስራዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ።

በጥቂት ዓመታት ውስጥም የሚታዩና ዓለም የመሰከረላቸው ውጤቶች መታየት ጀምረዋል።

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገውና የስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ምርትን በስፋት ማምረትን ግብ ያደረገው  'የሌማት ትሩፋት' መርሐ-ግብር ስርአተ ምግብን በማሻሻል የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ሁነኛ መንገድ ተደርጎ ተወስዷል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ ያለው ዓመታዊ የወተት ምርት 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር ሲሆን ዓመታዊ የወተት የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ደግሞ ከ66 ሊትር አይበልጥም፡፡

ለቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ዓመታዊ የወተት ምርትን ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር የማድረስ ግብ ተይዟል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የተቀነባበሩ የወተት ውጤቶችን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ በአማካይ የምታወጣውን ከ25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማስቀረትም ታቅዷል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት በአማካይ በዓመት 40 እንቁላል ብቻ የሚጥሉ ሲሆን፤ በዘመናዊ የዶሮ እርባታ በዓመት ከአንድ ዶሮ 270 እንቁላል የማምረት ሙከራዎችን ለማስፋት እንደሚሰራም የመርሐ ግብሩ እቅድ ያሳያል።

በተጨማሪም የዶሮ ስጋ ዓመታዊ ምርትን አሁን ካላበት 90 ሺህ ወደ 240 ሺህ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን ከ147 ሺህ ወደ 296 ሺህ ቶን ለማሳደግም ግብ ተይዟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ  "የሌማት ትሩፋት  ቤተሰብን ከመመገብ ባሻገር በምግብ ራሷን የቻለች አገር የሚገነባበት መርሐ ግብር በመሆኑ አመራሩና አርሶ አደሩ ሌት ተቀን ለስኬቱ መትጋት አለባቸው" ብለው ነበር።

ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጥ ፍቱን መድሃኒት ከመሆን ባለፈ ለሌማት ትሩፋት መሳካት አይነተኛ ሚና አለው።

በዚህም ከ2011 እስክ 2014 ዓ.ም በተተገበሩ አራት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች ለጥምር ደን እርሻ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለከተማ ውበት፣ ለመድሃኒት እና ለምግብ የሚውሉ 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።

አረንጓዴ አሻራ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያመጣው ችግር የተነሳ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በተደጋጋሚ የሚጎበኘውን ድርቅ ለመቋቋምም  ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና ሌማት ትሩፋት እያከናወነች ያለውን ተምሳሌታዊ ተግባር ጎረቤት አገራት ወስደው ከተገበሩት የቀጣናው አገራት በትብብር ከችግር መውጣት ይችላሉ።

ምክንያቱም የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ከደን ልማት ባሻገር የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ አካል ተደርጎ እየተተገበረ ያለ ሲሆን የሌማት ትሩፋት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብን እውን የማድረግ ትልቅ ሀሳብና ተግባር ነውና።

ለአብነትም ባለፉት ዓመታት የፍራፍሬ ችግኞችን የአረንጓዴ አሻራ አካል በማድረግ በትኩረት በመሰራቱ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ሁለተኛዋ የአቮካዶ አምራች ሀገር መሆኗንና በቀጣይ ሁለት ዓመታት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ለመሆን እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 02 ቀን 2015 ዓ.ም በየካ ተራራ የአፕል ችግኞችን በተከሉበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከተመጣጠነ ምግብ ጋር ያለው ቁርኝት የማይነጣጠል በመሆኑ እነዚህ ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው አይነተ ብዙ ነው።

በሌማት ትሩፋት ገበታን በተመጣጠነ ምግብ መሙላት ከተቻለ የእናቶችንና የህጻናትን ፍላጎት በማሟላት በአካል የዳበረና በአዕምሮ የበለጸገ ትውልድ መገንባት ይቻላል።

በተቃራኒው ያልተመጣጠነ አመጋገብ ጤና ላይ ከሚፈጥረው ችግር ባለፈ በሰዎች መካከል ያለውን የኑሮ አለመመጣጠን በማስፋት፣ ማህበራዊ ቀውስን በመፈልፈልና ኢኮኖሚውን በመጉዳት ምርትና ምርታማነትን ወደ ኋላ የሚጎትት ይሆናል፡፡

ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በከባድ ትግል ላይ የሚገኙ ሀገራትን የልማት ግስጋሴ በመግታት ቀድሞ ወደነበሩበት የድህነት አረንቋ እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙና እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ህፃናት ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት በዕድሜያቸው ልክ ዕድገት የማያስመዘግቡ ወይም የመቀንጨር ችግር ያለባቸው መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ለዚህ ነው በምግብ ራስን ከመቻል ጎን ለጎን የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ የሚሆነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የተመጣጠነ አመጋገብ ጉድለት ለመሙላት መንግሰት የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ እየሰራ ይገኛል፡፡

በርካቶቹ ፕሮግራሞች የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተዘረጉ ሲሆን በዚህም ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንገዱን መጥረግ ጀምረዋል፡፡

ፕሮግራሞቹ የተለያዩ ምግቦችን በገበታ ላይ ማካተት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ከተግባራዊ የልማት ስራዎች ጋር ያካተቱ ሲሆን አዲስ የአመጋገብ ባህልን የሚያለማምዱም ናቸው፡፡

ለአብነትም ምግቤን ከጓሮዬ በሚል በአነስተኛ ቦታ ጭምር ሰዎች የጓሮ አትክልት በማልማት መመገብ የሚችሉበትን ስርአት እንዲከተሉ ከማድረግ ጀምሮ በአንድ አካባቢ የተለመዱ ምግባዊ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆነ ምርቶችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እስከማላመድ የዘለቁ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ማንሳት ይቻላል።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያለውን ተለምዷዊ የአመጋገብ ስርአት በመቀየር ረገድ ከዚህ በላይ የአመለካከትና የተግባር ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ደግሞ  ዘመናዊ የግብርና ዘዴ፣ የሌማት ትሩፋትና የመስኖ ልማት ስራዎችን በአረንጓዴ አሻራ ተግባራት ማጀብ ተስፋ የተጣለበት ትልቁ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መንገድ ተደርጓል።

የመስኖ ልማት ስራዎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚኖራቸው ፋይዳ ባለፈ የማያቋርጥና ተመጣጣኝ ውሃ የሚፈልጉትን አትክልትና ፍራፍሬዎች በስፋት ለማምረት ዕድል የሚሰጡ ናቸው፡፡

ከጉድጓድ በሚወጣ ውሃ የሚከናወነው የመስኖ ልማት በሀገሪቱ በስፋት እየተተገበረ ሲሆን ከልማቱ ባሻገር በድርቅ የሚጠቁ እንስሳትን ሀይወት በመታደግ ድርብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ በመተግበር ላይ የሚገኘው የአነስተኛ መስኖ ልማት በአግባቡ ተግባራዊ ከተደረገ የዜጎችን ገቢና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ በዓመት ሁለቴ የሚከናወነውን ግብርና 365 ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ይህንን የሌማት ትሩፋትንና የመስኖ ልማት ተግባር ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እውነተኛ መፍትሄ በማለት ይገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2021 በኢትዮጵያ የተቋቋመው የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር የዘርፉን ግስጋሴ ያፋጠነ ሲሆን የኢትዮጵያን የልማት ስትራቴጂ ከግብ ያደርሳል ተብሎም ታምኖበታል፡፡ 

በኢትዮጵያ እየተተገበሩ የሚገኙ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራሞችና አነስተኛ የመስኖ እርሻዎች ዓመታዊውን የምግብ አቅርቦት ጉድለት በመሙላት፣ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የህጻናትን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማስገኘታቸውን ጥናቶች እያመላከቱ ነው፡፡

በአነስተኛ መስኖ የሚታገዙ የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቶች የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ የተመጣጣነ የምግብ ስርአት እንዲኖረው እያገዙ ይገኛሉ።

የሌማት ትሩፋት ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ በአገር ግንባታ ሂደት ወስጥ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያግዝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ከምግብ ዋስትና ጋር በማስተሳሰር አንድም ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች ሁለትም የዜጎችን ህይወት የሚቀይርና የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ተግባር እያከናወነች መሆኑ እሙን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በጣሊያን ርዕሰ መዲና ሮም በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ይህንኑ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።

የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች አፈርና ውሃን በመጠበቅ ለግብርና ስራ ምቹ ከባቢ በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ በመሆኑ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ስራ በአንድ ድንጋይ. . . ይሉትን አይነት ነው።

ክልሎችም የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ መርሃ ግብር በይፋ በማስጀመር እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው።

ይህም በአረንጓዴ አሻራ፣ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአፈር እና በውሃ ጥበቃ፣ በመስኖ ልማት የተጀመሩ አበረታች ስራዎችን በውጤት ለማጀብ ያግዛል።

የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና የቤተሰብ አቅም በመገንባት መሠረታዊ ውጤት የሚያመጣውን መርሃ ግብር በየደረጃው የሚገኙ ፈፃሚና አስፈፃሚ ተቋማትና ድጋፍ ሰጪ ማዕከላት ተቀናጅተው ሊተገብሩት ይገባል።

እንደ አገር የተጀመረውን አረንጓዴ አሻራ፣ የመስኖ ልማትና የሌማት ትሩፋት ስራዎች አሰናስሎ የመተግበር እንቅስቃሴ በቀጣይ ዓመታት በተከታታይ ማሳካት ከተቻለ በእርግጥም በምግብ ሉአላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትየጵያን ዕውን ማድረግ ይቻላል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም