ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጉዞ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 6/2015(ኢዜአ)፦ ሶስተኛው የካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ በኮትዲቭዋር አቢጃን በሕዳር ወር 2016 ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በአምስት ዞኖች 36 ክለቦች የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ከዞኖቹ መካከል አንዱ ሲሆን በዚህ ዞን ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ጨምሮ ዘጠኝ ክለቦች የሻምፒዮንስ ሊጉ ቦታውን ለማግኘት ይፋለማሉ።

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ዛሬ ይጀመራል።


 

በማጣሪያ ውድድሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ አንድ ከዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ፣ ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንስት ስታርስ እና ከጅቡቲው ፋድ ክለብ ጋር ተደልድሏል።

በውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ ጋር በንጄሩ ከተማ ‘FUFA Technical Center Stadium’ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከዚህ ቀደም በኬንያ እና ታንዛንያ በተካሄዱ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድሮች በቅደም ተከትል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

በምድብ አንድ የዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንት ስታርስ ጋር ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በዩጋንዳ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር በምድብ ሁለት የታንዛንያው ጄኪቴ ኩዊንስ፣ የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ፣ የሩዋንዳው ኤ ኤስ ኪጋሊ እና የዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽን ክለብ ተደልድለዋል።

የውድድሩ አሸናፊ ክለብ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።

የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ነሐሴ 24/2015 ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም