ቀጥታ፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማነት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል--አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ 

አሶሳ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ) የቱሪዝም ሚኒስቴር በሀገሪቱ እየተካሄደ ላለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማነት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አስታወቁ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብርን ዛሬ በአሶሳ ከተማ አስጀምረዋል።

ሚኒስትሯ በእዚሁ ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ እየተካሄደ ላለው የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር ስኬት የድርሻውን እየተወጣ ነው።

ለእዚህም ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ 200 አቅመ ደካማና ረጅ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬ የምግብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ድጋፉ የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይትና ማካሮኒን እንደሚያካትትም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በቀጣይም ለክልሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ አምባሳደር ናሲሴ አስታውቀዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ለድጋፉ ምስጋና አቅርበው፣ የክልሉ መንግስትም በወረዳ ደረጃ ለሚከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

"በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ረገድ ሰፊ ሥራ ይጠብቀናል" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ነገም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በባንባሲ፣ በአብራሞ እና በኡራ ወረዳዎች የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳት የማስጀመር ሥራ ይከናወናል።

ወላጆቻቸው አቅም ለሚያንሳቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በአብራሞ ወረዳ ለሚገነባው መለስተኛ ቤተ መጻህፍት የመሠረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ተገልጿል።

በተጨማሪም የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማቱ አመራሮች ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን እንደሚያኖሩ ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም