ቀጥታ፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ አበረታች ሥራዎች ቢሰሩም ተጨማሪ ትኩረትና ቅንጅታዊ ሥራ ያስፈልጋል--ዶክተር እንዳለ ሃይሌ

አዳማ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ)፡- ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ አበረታች ሥራዎች ቢሰሩም ችግሮቹን ለማስቀረት የአስፈጻሚ አካላት ትኩረትና ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ አስገነዘቡ።

ተቋሙ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአራት ክልሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረትና የህፃናትና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በአስፈፃሚ አካላት በተሰሩ ሥራዎች ላይ ያደረገውን የቁጥጥር ውጤት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እንደገለጹት፣ ተቋሙ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንጻር በጤና ተቋማት በተሰሩ ሥራዎች ላይ የቁጥጥር ስራ አከናውኗል።

በተጨማሪም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛትና ሌሎች መሰል ድርጊቶችን ከማስቀረት አኳያ በአስፈፃሚ አካላት የተከናወኑ ሥራዎችና ያሉ ክፍተቶችን የመለየት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል። 

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ አበረታች ሥራዎች ቢሰሩም ችግሮቹን በሚፈለገው መጠን ለማስቀረት ተጨማሪ ትኩረትና ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚፈልግ ዶክተር እንዳለ አስገንዝበዋል።

መድረኩ በቁጥጥር ሥራው ግኝትና በቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በተቋሙ የሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለወርቅ ታሪኩ በበኩላቸው በ2015 በጀት ዓመት ተቋሙ ዘጠኝ የቁጥጥር ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል። 

"በተለይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በ2017 ዓ.ም ለማስቆም የተያዘውን ግብ ለማሳካት በአስፈፃሚ አካላት በኩል አበረታች ሥራዎች ቢሰሩም ግቡን የሚያሳኩ አይደሉም" ብለዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና መሰል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሁንም እየተፈጸሙ መሆኑን በቁጥጥር ወቅት መለየታቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ከመቀነስ አኳያ በጤና ተቋማትና በጤና ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎች ላይ ቁጥጥር መደረጉን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በዚህም የእናቶች የቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ የጤና አገልግሎት የተሻለ ሥራ የተሰራበት ቢሆንም የደም አቅርቦት፣ የአምቡላንስ እና የማሞቂያ ማሽኖች እጥረት መስተዋሉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከጤና ባለሙያዎች እና ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን በቁጥጥር ሥራው መለየቱን ነው ወይዘሮ ሰብለወርቅ ያስታወቁት።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በሲዳማ ክልል የጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ትኩረት የሚሹ ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የተሰሩ ሥራዎችና ያሉ ክፍተቶችን በተመለከተ በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የቁጥጥር ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም ችግሮች እንዳሉ መለየቱን ገልጸው፤ "በተለይ ግርዛት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና መሰል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሁንም እየተስተዋሉ በመሆኑ የአስፈጻሚ አካላት ትኩረትና ቅንጅታዊ ርብርብ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው መድረክ ከጤና፣ ከሴቶች፣ ከህብረተሰቡ የተወከሉ ተሳታፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም