የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም መርሃ ግብርን ለማሳካት የግሉ ዘርፍ በንቃት መሳተፍ አለበት - የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም መርሃ ግብርን ለማሳካት የግሉ ዘርፍ በንቃት መሳተፍ አለበት - የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ) ፦ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም መርሃ-ግብር በስኬት እንዲጠናቀቅ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢንሼቲቭ አፍሪካ ጋር በመተባበር በፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት መሠረት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የግሉን ዘርፍ ሚና በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም ሀገራት የተሳካ የመልሶ ማቋቋም ስራ አከናውነዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ያለው የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለስ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ኮሚሽኑ ባለፉት ሰባት ወራት ከሁሉም ክልሎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ለይቷል ብለዋል፡፡
እነዚህ የተለዩ የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ በመንግስት ገንዘብ ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ የለጋሽ ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በዓለም ላይ ያለው ልምድ የሚያሳየው ስኬታማ የመልሶ ማቋቋም ስራ የተከናወነው ከመንግስት በተጨማሪ ህብረተሰቡን፣ የግልና ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማሳተፍ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የግሉ ዘርፍ በገንዘብ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በስልጠና እና በቴክኒክ ድጋፍ ለመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ ስኬታማነት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሐፊ ዶክተር ደገላ ኤርገኖ፤ መንግሥት የጀመረውን የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር የግሉ ዘርፍ መደገፍ እንዳለበት ገልጸዋል።
መንግስት ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የጀመረው ሀገራዊ የመልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብር የግሉ ዘርፍ በባለቤትነት ሊሳተፍበት እንደሚገባም ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንደ ተቋም የቴክኒክና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ከመደገፍ ባለፈ፤ የግሉ ዘርፍ በሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ጉዳዮች ሀገራዊ ግዴታችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ የጋራ ልማትና ትብብር ኃላፊ ኦሳ አንደርሰን በበኩላቸው፤ የቀደሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት የጀመረው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በግጭቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙና የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ከመንግሥት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍና ለጋሽ ድርጅቶች ሚና የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ የገንዘብ፣ የአቅም ግንባታ፣ የክህሎት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የስዊድን መንግሥትም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢንሼቲቭ አፍሪካ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ በጦርነቱ የተሳተፉ ወጣቶች በድህረ ጦርነት ራሳቸውን ችለው መደበኛ ህይወት መምራት እንዲችሉ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ከብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን እና ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር የውይይት መድረክ በማዘጋጀት መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡