ሰራዊቱ በጽንፈኛ እና በዘራፊ ቡድኑ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ከተሞች ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ ህዝባዊ ባህሪውን እና መከታነቱን በተግባር አረጋግጧል--የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ በጽንፈኛ እና በዘራፊ ቡድኑ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ከተሞች ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ ህዝባዊ ባህሪውን እና መከታነቱን በተግባር አረጋግጧል--የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ) ፦ ሰራዊቱ በጽንፈኛ እና በዘራፊ ቡድኑ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድና ከተሞች ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ ህዝባዊ ባህሪውን እና መከታነቱን በተግባር ማረጋገጡን የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እና የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያው ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሰራዊቱ ባከናወነው የህግ ማስከበር ተግባር የአማራ ክልል ከተሞች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
ሰራዊቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሰራው ስራ ውስጥ ህዝቡ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ከተሞቹ ከስጋት ነጻ መሆን መቻላቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገልጸዋል።
በዚህም ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ የአውሮፕላን በረራ ወደ ባህርዳር፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ከተሞች መጀመሩንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የመንግስት እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ የመጀመሪያ ተግባሩን በስኬታማነት አጠናቆም ወደ ሁለተኛው ተግባሩ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል።
አንዳንድ አካላት ህዝባዊ ባህሪ ያለውን የመከላከያ ሰራዊት ስም ለማጠልሸትና ለማጥፋት ከሚያደርጉት ጥረትም ሊቆጠቡ ይገባልም ብለዋል።
ጽንፈኛ ቡድኑ አገርን ለማፍረስ በማሰብ ሁሉን ሁኔታ መጠቀሙን ገልፀው ህዝብን መዝረፍ፣ መንገድ መዝጋት፣ አመራሮችን መግደል እና ሌሎችንም እኩይ ተግባራት ማከናወኑንም ጠቁመዋል።
ቡድኑ መንገዶችን በመዝጋትም ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ጋር እንዳይደርስ የማድረግ እኩይ ተግባር ማከናወኑንም ገልጸዋል።
መንግስት ለሰላም አማራጭ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ እንደነበርም ጠቁመዋል።