የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት 23 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት 23 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ)፦ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ እንደገለጹት በአማራ ክልል ካለው የጸጥታ መድፍረስ ጋር ተያይዞ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቀጥታም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ከዚህ ጽንፈኛና ዘራፊ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸውና የጥፋት ድርጊቱን የማቀጠጣል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ጽንፈኛና ዘራፊ ቡድኑን በከተሞች በመሆን በሚዲያ፣ በሎጂስቲክና በመረጃ ሽፋን በመስጠት የደገፉና የተወሰኑ ደግሞ ለከተማ ግዳጅ የተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ 23 ተጠርጣሪዎች ብቻ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው በክልሉ መጠነ ሰፊ እስር እየተካሄደ ነው የሚባለው አሉባልታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ ግለሰቦች መያዝ፣ ማሰርና ማንገላታት እንዲሁም ሌሎች የዲሲፕሊንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከተፈጸሙ ኮማንድ ፖስቱ እያጣራ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
የተለያዩ የኦፕሬሽን ሥራዎች በአራቱም የአማራ ክልል ቀጠናዎች ተጠናክሮ መጠቀሉን ገልጸው በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላትን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።
የምርመራና የክስ ሂደቱ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከመከላከያና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በጋራ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።