ቀጥታ፡

በ2016 በጀት ዓመት የዋጋ ንረትን ከ20 በመቶ በታች ለማድረግ ታቅዷል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ)፡- በ2016 በጀት ዓመት የዋጋ ንረቱን ከ20 በመቶ በታች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።  

በመግለጫቸውም የዋጋ ንረት ባለፉት ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ የዋጋ ንረቱ 29 በመቶ እንደሆነ ለአብነት ጠቅሰው፤ ይህም በኅብረተሰቡ የዕለት ተለት ኑሮ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል።  

የዋጋ ንረትን መዋጋት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ያሉትን የፖሊሲ መሳሪያዎች በመጠቀም የዋጋ ንረትን ለማቃለል መንግሥት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል። 

ይህንንም ተከትሎ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ውሳኔ ማድረጉን ነው የገለጹት።

በዚህም የግብርና ምርቶችን ትርጉም ባለው መልኩ በመጨመር አቅርቦትን ማሻሻል፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን የሚያሳልጡ መዋቅራዊና የፊስካል ፖሊሲ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል። 

በተያዘው በጀት ዓመት ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና የዋጋ ንረትን ለማርገብ የመንግሥት ወጪ እድገት እንዲገደብና የበጀት ጉድለቱም ከጠቅላላ አገራዊ ምርት አኳያ እንዲቀንስ ግብ መያዙን ጠቁመዋል። 

በዚህም መሠረት ለመንግሥት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር በእጅጉ በመቀነስ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰጠው ብድር ከአንድ-ሦስተኛ (ሲሶ) እንዳይበልጥ ይደረጋል ብለዋል። 

የገንዘብ ሚኒስቴር ቀጥታ ብድርን እንደ መጨረሻ አማራጭ የሚጠቀመው የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ በበቂ መጠን ለገበያ መቅረብ ሳይችል ሲቀር ብቻ እንደሚሆን መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።   

ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ ከሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ የብድር አቅርቦት ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑን ጠቁመዋል።  

ቁልፍ የሆኑ የወጪ ንግዶች ላይ የተሰማሩ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ላኪዎች የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል መደረጉንም እንዲሁ። 

የአገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ ገደብ እንደሚደረግበት ገልፀዋል።

በዚህም መሠረት ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸው በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም ባንኩ የዋጋ ንረትን በ2016 በጀት ዓመት ከ20 በመቶ በታች እንዲሁም በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማድረስ ይሰራል ነው ያሉት።

የዋጋ ንረትን ማርገብ የአንድ ተቋም ኃላፊነት እንዳልሆነ የተናገሩት የባንኩ ገዥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለፖሊሲ እርምጃዎች ተፈጻሚነት የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም