ቀጥታ፡

ካሊክስ ኬሚካልስ እና ፋርማሲዩቲካልስ የተሰኘ የህንድ ግዙፍ ኩባንያ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ)፡- ካሊክስ ኬሚካልስ እና ፋርማሲዩቲካልስ የተሰኘ የህንድ ግዙፍ ኩባንያ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማምረት ያለውን ፍላጎት ገልጿል።

ኩባንያው ለአለም 60 በመቶ የሚሆነውን የወባ እና የሳንባ ነቀርሳ መድሀኒት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የሚያቀርብ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የኩባንያው ተወካዮችን ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም ኩባንያው ስለ ኢንቨስትመንት እቅዱ ያለውን ዝርዝር ሀሳብ በተመለከተ የኩባንያው ተወካዮች ለዋና ስራ አስፈፃሚው ማቅረባቸው ተገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ኢንቨስትመንቱ በፍጥነት እውን እንዲሆን ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዋና ስራ አስፈጻሚው ለተወካዮቹ በማረጋገጥ ቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

ኩባንያው በአለም 60 በመቶ የሚሆኑ ለወባ እና ለሳንባ ነቀርሳ መድሀኒት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የሚያመርት ድርጅት መሆኑ በመረጃው ተመላክቷል።

የኩባንያው መቀመጫ ህንድ ሲሆን በአለም ላይ ያሉ ግዙፍ መድኃኒት አምራቾች ለምርት ሂደት የሚጠቀሙባቸውን ግብዓቶች ከዚሁ ኩባንያ እየተረከቡ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም