የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ የለውጥ ሂደትን የሚያፋጥን የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ የለውጥ ሂደትን የሚያፋጥን የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ የለውጥ ሂደትን የሚያፋጥን የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የሚያደርገው ያልተቋረጠ ጥረት የሚደነቅ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
ዩንቨርሲቲው ሲያከናውን የቆየውን ሁለንተናዊ የተቋማዊ ሪፎርም ስልጠና አጠናቋል።
በማጠቃለያ መርሐ -ግብሩም የማዕረግ ማልበስ፣ በስራቸው የላቀ ብልጫ ላሳዩ አመራርና አባላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።
የአየር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንዳሉት የተቋማዊ ለውጥ ሂደት አፋጣኝ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ እየተጫወተ የሚገኘው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
መከላከያ እንደ ተቋም በሁለንተናዊ ለውጥና ፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታን በመደገፍ ረገድ አሁን እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ያሳሰቡት ሌተናል ጄኔራል ይልማ ተመራቂዎች ያገኙትን ዕውቀት በተግባራዊ ስራቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዋና አዛዡ ለማዕረግተኞችም መልካምና ውጤታማ የስራ ዘመን ተመኝተው በላቀ የሃላፊነት ስሜት የመሪነት ሚናቸውን መጫወት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ተገቢ ሚናውን መጫወት እንዲችል ያለፈውን በጀት ዓመት አፈጻጸም በደንብ በመፈተሽ ለቀጣዩ የ2016 በጀት ዓመት ለላቀ ውጤት መዘጋጀት የሚያስችለውን አቅም አጎልብቷል ብለዋል።
ኮማንዳንቱ ከመማር ማስተማር ተቋማዊ ሃላፊነት ባሻገር የአካባቢ ማህበረሰብን አኗኗር በሚያሻሽሉ የጥናትና ምርምር ተጨባጭ ድጋፎች ላይም በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያመላከቱት።
በስልጠናው የተሳተፉ የሰራዊት አባላትና ሲቪል ሰራተኞች የተሰጣቸው የማዕረግ እድገትና ሽልማት እንዳስደሰታቸውና በበለጠ ኃላፊነት ለመስራት እንዳነሳሳቸው ጠቅሰው ያገኙትን የስልጠና አቅም በመደመር በቀጣዩ የስራ ጊዜያት ተግተው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።