ቀጥታ፡

19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ የሚኒስትሮች ጉባኤ በመጪው ሣምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015(ኢዜአ)፦ 19ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃ የሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ በመጪው ሣምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለፀ።

ጉባኤው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት "የአፍሪካን የአካባቢ ችግሮችን ለመፍታት ዕድሎችን መጠቀም፣ ትብብርን ማጎልበት” በሚል መሪ ኃሳብ ነሐሴ 11 እና ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

በጉባኤው ከመላው አፍሪካ የተወጣጡ ከ40 በላይ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ጨምሮ ከ440 በላይ ተሳታፊዎች በጉባኤው እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

ጉባኤውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጉባኤው የዘርፉን ዓለም አቀፍ ትብብር ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቱ እያጋጠሙ ያሉ የአካባቢ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተዘጋጁ ዓለም አቀፋዊ የአካባቢ ጥበቃ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ልምዷን ለሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደምታጋራ ገልጸው ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈር ተናግረዋል።

ከዋናው የአከባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ጉባኤ አስቀድሞ የባለሙያዎች ቡድን፤ ሚኒስትሮቹ በሚወያዩበት አጀንዳዎች ላይ የሚመክር መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም