ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውኃ ኃብት ላይ የሚሰሩ የዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች በቋሚነትና በተቀናጀ አግባብ ሊሰሩ ይገባል - የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የውኃ ኃብት ላይ የሚሰሩ የዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች በቋሚነትና በተቀናጀ አግባብ ሊሰሩ እንደሚገባ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።

ዘጠነኛው የውሃ፣ የውኃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ፎረም 'ጠንካራ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ለዘላቂ የውኃ ልማት' በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመስኩ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመርኃ ግብሩ ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከባሕርዳር፣ ከአዳማ፣ ከጅማና ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሠነድ ሥምምነት ተፈራርሟል።

ዶክተር ኢንጂነር ኃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የውኃ ዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽን በባለሙያዎች መመራት እንዳለበት ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቷል።

የውኃ ዲፕሎማሲና ኮሙኑኬሽን በተቋማት ደረጃ መመራት እንዳለበት ጠቅሰው የዘርፉ አካላት ሥራውን በቋሚነትና በቅንጅት መሠራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ከዚህ አንጻር በውኃ መስክ አቅም በመገንባት ዩኒቨርሲቲዎች ትልቁን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመው ተቋማቱ በውኃ ኃብት ላይ ውጤታማ ምርምር መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የውኃ ጥያቄዎች የፖለቲካ ሳይንስና የዲፕሎማሲ ባለሙያዎች አጀንዳ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድም ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የሚሰራውን ሥራ ያጠናክራል ብለዋል።


 

በየተቋማቱ የሚሰሩ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን በተደራጀ መልኩ ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠይቅ ጠቁመው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራውም ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም