አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015(ኢዜአ)፡- ቀድሞ አይካ አዲስ ተብሎ ይጠራ የነበረውና በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ቡሉኮ ኢንቲግሬትድ ጨርቃጨርቅ የሚል ስያሜ ያገኘውን ፋብሪካ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች በፋብሪካው ጉብኝት አድርገው ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተወያይተዋል።
አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላለፉት 4 ዓመታት ስራ አቁሞ የነበር ሲሆን በስሩ ከ7 ሺህ በላይ የስራ ዕድል የፈጠረ እና ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የነበረው ፋብሪካ እንደነበረ ተገልጿል።
የከፍተኛ አመራሩ የመስክ ጉብኝት ዋና አላማም ፋብሪካው ከሚፈጥረው በርካታ የስራ ዕድል በተጨማሪ ለሀገር የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ዳግም ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ ነው፡፡
በተጨማሪም ፋብሪካውን በአዲስ መልክ ወደ ስራ ለማስገባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍና አስፈላጊውን እገዛ ማድረግም የጉብኝቱ አላማ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ፋብሪካውን የኦሮሚያ የልማት ድርጅት ከግል ከባለሀብቶች ጋር በመሆን ወደ ስራ ለማስባት እየሰሩ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
በሚኒስቴሩ የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ የተዘጉና ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርገውን የድጋፍና ክትትል ማዕቀፍ መሰረት በማድረግ አስፈላጊው ድጋፍ ለፋብሪካው እንደሚደረግም ተጠቁሟል።