ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዩጋንዳ በተካሄደው የአፍሪካ የቡና ጉባኤ ላይ ተካፈሉ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዩጋንዳ በተካሄደው የአፍሪካ የቡና ጉባኤ ላይ ተካፈሉ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 5/2015 (ኢዜአ)፡- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዩጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው ሁለተኛው ‘G-25’ የአፍሪካ የቡና ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ጉባኤው ከነሐሴ 1 እስከ 4/2015 “የአፍሪካ የቡና ዘርፍ እሴትን በመጨመር ማሳደግ” በሚል መሪ ሀሳብ የተከናወነ ነው።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መሪዎች፣ በአህጉሪቷ የሚገኙ የዘርፉ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የቡና አምራቾችና ላኪዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በዚህ አህጉራዊ ጉባኤ ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ኢዜአ በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጉባኤው በአፍሪካ ቡና አምራች በሆኑ አገራት የሚገኙ አምራቾች እሴት ጨምረው ቡና በመላክ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያላት ድርሻ ማሳደግና ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው መንገዶች ላይ መክሯል።
የቡና አምራቾች እና የዘርፉ ተቋማት የማይበገር የግብርና ስርዓት በመገንባት የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት መወጣት በሚገባቸው ሚና ላይ ውይይት ተደርጓል።