ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን በጎረቤት አገራት ለማስፋት የምታደርገው ጥረት የመስኩን የትብብር ዲፕሎማሲ ያጠናክራል - ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/2015 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን በጎረቤት አገራት ለማስፋት የምታደርገው ጥረት የመስኩን የትብብር ዲፕሎማሲ እንደሚያጠናክረው የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ተናገሩ።      

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር የገጠሟትን የደን መጨፍጨፍና አየር ንብረት ለውጥ ለመቀልበስ ሁሉን አቀፍ ርብርብ በማድረግ ላይ ትገኛለች።    

በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት አራት ዓመታት ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል። 

በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብርም ተጨማሪ 25 ቢሊየን ችግኝ የመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መፍትሔ ያስፈልገዋል በሚል መርህም ከራሷ አልፎ አረንጓዴ አሻራ በጎረቤትና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በስፋት እንዲተገበር ቁርጠኛ አቋሟን አሳይታለች።      

ይህንንም ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት ወጣቶች በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ አገራት "ወንድማማችነትን እንትከል" በሚል መሪ ኃሳብ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሮችን ማካሄዳቸውም ይታወሳል። 

ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብርም ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሁነኛ መፍትሔ በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የባንዲራ ፕሮጀክት እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። 

የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ የገባችውን ዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ስምምነትን በማስፈጸምና የሚጠበቅባትን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆኗን ጠቁመዋል። 

ጎን ለጎንም በአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር የጎረቤት አገራትን ለማሳተፍ የጀመረችው ጥረት የመስኩን የትብብር ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ወደፊት በማምጣትና በማስተግበር ያላትን የመሪነት ሚናዋን የሚያስቀጥል መሆኑን ነው ያነሱት። 

ኢትዮጵያ በስፋት እያካሄደች ያለው አረንጓዴ አሻራ በተለይም ለአረንጓዴ ዲፕሎማሲው እንዲሁም ለአገሪቱ አጠቃላይ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑንም አብራርተዋል። 

በመሆኑም አገሪቷ ችግኝ ተከላዎችን ማጠናከርና ሌሎችም የአፍሪካ አገራትን በመርሃ-ግብሩ በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ የሚጠበቅባትን ሚና ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባት ነው ያነሱት። 

ከዓመታት በፊት ከ3 በመቶ በታች የነበረው የደን ሽፋን አሁን ላይ ከ15 በመቶ በላይ መድረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

 

 

   

 

 

 

 

 

 

 

    

 

 

        

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም