የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመጪው ዓመት ከ300 በላይ ስፖርተኞችን ሊያሰለጥን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመጪው ዓመት ከ300 በላይ ስፖርተኞችን ሊያሰለጥን ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በ2016 ዓ.ም ከ300 በላይ ስፖርተኞችን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለአራት ዓመታት እንደሚያሰለጥን የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው ተናገሩ።
በሥልጠናው የሚሳተፉ ስፖርተኞች እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች መሆን እንዳለበት ተጠቅሷል።
ስፖርተኞቹ በአራት ዓመት ቆይታቸው በሳይንስ የታገዘ ዘመናዊ ሥልጠና እንደሚሰጣቸውም እንዲሁ።
ይህንንም ተከትሎ ስፖርተኞቹን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመመልመል ሥራ ከነገ ጀምሮ በሁለት ዙር እንደሚካሄድ ነው የተጠቆመው።
የመጀመሪያ ዙር ከነገ ነሐሴ 5 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲሁም ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከነሐሴ 20 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሏል።
አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ቮሊቦል፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና ቅርጫት ኳስ አካዳሚው ምልመላ ከሚያደርግባቸው የስፖርት ዓይነቶች መካከል ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አካዳሚው በመጪው ዓመት 307 ስፖርተኞችን ተቀብሎ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ያሰለጥናል።
ስፖርተኞቹ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ አካዳሚው ባስቀመጠው መስፈርት የሚመለመሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አካዳሚው ለቀጣዩ ዓመት ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ብዙ ሰልጣኞች እንደሚቀበል አስታውሰው፤ ይህም በዋናነት በዘርፉ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት ተከትሎ መሆኑን ገልፀዋል።
በታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድን አገሪቱን በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ከሚወክሉ ስፖርተኞች አብዛኛዎቹ የአካዳሚው ፍሬ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያን የወከለው አትሌት ሰለሞን ቱፋ እና በ3 ሺህ መሰናክል የዓለም ክብረወሰን የሰበረው ለሜቻ ግርማ በአካዳሚው ያለፉ ተጠቃሽ ስፖርተኞች ናቸው።
ከስምንት ቀን በኋላ በሃንጋሪ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በ3 ሺህ መሰናክል የሚወክሉት የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት ለሜቻ ግርማን ጨምሮ ጌትነት ዋለና አብርሃም ስሜ ይገኙበታል።
በሥልጠናው የሚሳተፉ ታዲጊ ስፖርተኞች ብቃታቸው ተረጋግጦ ወደ ሥልጠናው እንደሚገቡ ገልጸዋል።
አቅሙ ያላቸው ስፖርተኞች የሥልጠና ዕድሉን እንዲጠቀሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።