ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ትሰራለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/2015 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማስፋት የጀመረችውን ተግባራት አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ በውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት እየሰራች ነው ብለዋል።

በዚህም በባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ አገራት ተወካዮች በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ባለፈው ሳምንት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፣ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ናሌዲ ፓንዶር፣ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሺማሳ ሃያሺ እና የኮሪያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ የኢትዮጵያ ጉብኝትም የዚሁ የውጤታማ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በዓለም ባንክ በኩል ኢትዮጵያን በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራ ላይ ለማገዝ ፍላጎት እንዳለ የተገለፀበት መሆኑን አምባሳደር መለስ ጠቁመዋል።

እነዚህ ጉብኝቶች በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ የተሰራበት መሆኑን አመላካች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የማስገንዘብ፣ ወዳጅ የማብዛትና የማለዘብ ሥራ አንዱ አካል መሆኑን ገልፀው ይህ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም