ለሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ስድስት ወራት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል - የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ለሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ስድስት ወራት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል - የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/20115 (ኢዜአ) ፡- ለሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ስድስት ወራት ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ገለጹ።
በኢትዮጵያ በቅርቡ ገቢራዊ በተደረገው ከአገር በቀል የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ አንዱ በመንግሥት ብቻ ሲቀርብ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት በማሻሻል ለዓለም አቀፍ አቅራቢዎች ክፍት ማድረግ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ተቋማት ፈቃድ ለመስጠት ቀደም ሲል ጨረታ ወጥቶ በኬንያው ሳፋሪኮም የተመራው ጥምረት በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያውን ፈቃድ መውሰዱ ይታወሳል።
በጨረታው ላይ ተሳትፎ የነበረው ኤም ቲ ኤን ግሩፕ በወቅቱ አቅርቦት የነበረው ገንዘብ ከሳፋሪኮም አንጻር ልዩነቱ በመስፋቱ የሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ መቅረቱንም ነው የባልሥልጣኑ መረጃ የሚያሳየው።
አሁን ላይ ደግሞ ሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር በምን መልኩ መንቀሳቀስ አለበት የሚለውን ለመወሰን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ነው የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ለኢዜአ የገለጹት።
በዚህም መሰረት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለሦስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋም ፈቃድ ለመስጠት የብቃት መጠየቂያ ሰነድ መውጣቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ይህንን የብቃት መጠየቂያ ሰነድ ሞልተው እስከ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲያስገቡ ቀነ ገደብ መቀመጡንም ጠቁመዋል።
ከዚህ በኋላ በሂደቱ የተለዩት ኩባንያዎች የሃሳብ እቅድ (Proposal) እንዲያስገቡ ከተደረጉ በኋላ በመጨረሻም ሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር እንደሚለይ ገልጸዋል።
እነዚህ ሂደቶች ተጠናቅቀው የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ስድስት ወራት ለሦስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን አብራርተዋል።
የቴሌኮም ሴክተሩ ክፍት መደረጉ በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ በዋጋ ተመጣጣኝነት እንዲሁም በተደራሽነት በኩል ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልፀዋል።
የቁጥጥር ማዕቀፉ የአገሪቱን ደኅንነት ባስጠበቀ መልኩ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል።