የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ዩጋንዳ አቀና - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ዩጋንዳ አቀና
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ዩጋንዳ ያመራል።
ለሶስተኛ ጊዜ በኮትዲቯር አቢጃን በሚካሄደው የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ለመሳተፍ በአምስት ዞኖች 36 ክለቦች የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዞን ውስጥ ከተደለደሉት ዘጠኝ ክለቦች መካከል አንዱ ነው።
የዞኑ የማጣሪያ ውድድር በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከነሐሴ 6 እስከ 24/2015 ድረስ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ዩጋንዳ እንደሚያቀና ኢዜአ ከንግድ ባንክ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለውድድሩ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በሃዋሳ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
በማጣሪያ ውድድሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በምድብ አንድ ከዩጋንዳው ካምፓላ ኩዊንስ፣ ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ፣ ከደቡብ ሱዳኑ ዬ ጆይንስት ስታርስ እና ከጅቡቲው ፋድ ክለብ ጋር ተደልድሏል።
የመጀመሪያ ጨዋታውን ቅዳሜ ነሐሴ 6 2015 ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ ጋር ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከዚህ ቀደም በኬንያ እና ታንዛንያ በተካሄዱ የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድሮች በቅደም ተከትል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆኑ ነው።
በዩጋንዳ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር በምድብ ሁለት የታንዛንያው ጄኪቴ ኩዊንስ፣ የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ፣ የሩዋንዳው ኤ ኤስ ኪጋሊ እና የዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽን ክለብ ተደልድለዋል።
የውድድሩ አሸናፊ ክለብ የሴካፋ ዞንን ወክሎ በካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።
የኬንያው ቪሂጋ ኩዊንስ እና የታንዛንያው ሲምባ ኩዊንስ ከዚህ ቀደም በሞሮኮና በግብጽ በተካሄዱ የካፍ የሴቶች የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ሴካፋን ወክለው መሳተፋቸው ይታወቃል።