የሰላም እሴት ግንባታን እና የሰላም ጉዳዮችን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ለማካተት ዝግጅት እየተደረገ ነው - የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም እሴት ግንባታን እና የሰላም ጉዳዮችን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ለማካተት ዝግጅት እየተደረገ ነው - የሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/2015 (ኢዜአ)፦ የሰላም እሴት ግንባታን እና የሰላም ጉዳዮችን በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋሙ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ለፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸሙን አቅርቦ አስገምግሟል።
በግምገማው የሰላም ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት ሰላምን ለማጽናትና እሴቶችን ለመገንባት ያከናወናቸውን ቁልፍ ተግባራት አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።
ሚኒስቴሩ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ውይይቶች መደረጋቸዉን የገለጸ ሲሆን በነዚህ መድረኮች 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የሰላም ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ መካሄድ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሰላም ክበባት ውስጥ መታቀፋቸው እንዲሁም በአገሪቱ ከ42 ሺህ 500 በላይ በጎ ፈቃደኞች ከአካባቢያቸው ውጭ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለበጎ ፈቃድ ስራ መሰማራታቸውን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገልጸዋል።
ይህም የአብሮነት እሴትን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለውና ሚኒስቴሩ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቅ ስራ በጅምር ደረጃ መተግበሩንና ሚኒስቴሩ በበጎ ፈቃድ ስራ ዘርፍ የተሰራው ስራ ማምጣቱንና ይህም አገራዊ እሴቶችን ከማጠናከር አንጻር ውጤታማ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸዉ የተጀመሩ የሰላም አደረጃጀት ለውጥ እያመጡ መሆናቸውንና ተግባራቱ በልዩ ትኩረት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በአገር ግንባታ የልሂቃን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አንስተዋል።
በአንጻሩ በክልል መንግስታት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሁም ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ሚኒስትሯ መግለጻቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።