ቀጥታ፡

ሩሲያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ የትብብር ስምምነቶች አድርጋለች-አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2015 (ኢዜአ)፦ በሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ሩሲያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ የትብብር ስምምነቶችን ማድረጓን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ። 

በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ከሳምንት በፊት በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የተደረገውን ሁለተኛው የሩስያና አፍሪካ ጉባዔ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጉባኤው ስኬታማ ነበር ያሉት አምባሳደሩ፤ የአፍሪካ እና ሩሲያን ትብብር የሚያሳልጡ ስራዎች የተከናወኑበትና በአጠቃላይ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የተከፈተበት ነው ብለዋል።

ሩሲያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት ያሳየችበትና ግንኙነቷን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች የተደረጉበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በአፍሪካና በሩሲያ መካከል የንግድ ትስስር ከማጠናከር ባሻገር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በምግብ ዋስትና፣ በትምህርትና በኃይል ልማት ዘርፍ ከሀገራትና ቀጣናዊ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች  መደረጋቸውን አውስተዋል። 

ኢትዮጵያና ሩሲያ ከጉባኤው ጎን ለጎን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

ስምምነቶቹ በመተማመን ላይ የተመሰረተውን የኢትዮ-ሩሲያ ታሪካዊ ግንኙነትና ትስስር ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።


 

የአገራቱን የንግድ ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸው፤ በንግድ እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን በጋራ በመቅረፍ የተጀመረውን የንግድ ትስስር ለማሳለጥ ሩስያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

አምባሳደር ተረክሂን አክለውም በሶቬት ህብረት ዘመን በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ነፃ የትምህርት ዕድል መሰጠቱን አስታውሰዋል።

ሩሲያ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት ዕድል ማሳደጓንም ነው የተናገሩት።

ይህም የተማረ የሰው ኃይል ግንባታን ለማጠናከር ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር፤ ለኢትዮ-ሩሲያ የባህል ዲፕሎማሲ መጠናከር አይተኬ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

በሁለቱ አገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ጠንካራ የትምህርት ትብብር እንዲመሰረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የሩሲያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ዕድል እንደሚመቻች ገልፀዋል።

  በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍም በሁለቱ ሀገራት መካከል ትብብር መጀመሩን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በሩሲያው ዜና አገልግሎት ስፑቲኒክ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ለአብነት አንስተዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም