ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ዶክተር አለሙ ስሜ 

ጅግጅጋ ፤ነሐሴ 3/2015(ኢዜአ) ፡-  ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ  በትኩረት እየተሰራ  መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  ዶክተር አለሙ ስሜ  ገለጹ።   

ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ፣ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ቢሮዎች ጋር የ2015 በጀት አመት የእቅድ አፈፃፀምና የተያዘውን የስራ ዘመን እቅድን  ገምግሟል። 

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ  ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ እንዳሉት ፤ ትራንስፖርት ለኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ ግንኙነት ወሳኝ ነው።

ዘርፉንም   በምስራቅ አፍሪካ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ትራንስፖርት  ገጠሩን ከከተማ፣ ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማገናኘት እና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር  ሚና እንዳለው ተናግረዋል።


 

ይህን እውን ለማድረግ  መሠረተ ልማት የማስፋፋት ፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን የማሻሻል፣ የጭነት ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት የገቢና ወጪ ዕቃዎችን የወደብ ላይ ቆይታ የመቀነስ፣ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋንን ማሳደግ ላይ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን   ጠቅሰዋል። 

በሌላ በኩል የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥርና ህግ የማስከበር እንዲሁም የሎጂስቲክስ አገልግሎት ማዘመን ላይ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በአቪዬሽን ዘርፍ የተሻሻለና ተደራሽ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት ሰራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ  ከሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት ፣ከሁሉም ክልሎችና  ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ አመራሮችና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም