ቀጥታ፡

የህንድ-አፍሪካ አይሲቲ ኤክስፖ በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት እውቀትና ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል የሚፈጥር ነው -የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2015(ኢዜአ)፡- የህንድ-አፍሪካ አይሲቲ ኤክስፖ በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት እውቀትና ልምድ  እንዲቀስሙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከህንዱ ቴሌኮም ኢኩዩፕመንት እና አገልግሎት ጋር በመተባበር ዘጠነኛውን የህንድና አፍሪካ አይሲቲ ኤክስፖን አስጀምረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የህንድና አፍሪካ አይሲቲ ኤክስፖ 30 የህንድ አይሲቲ ኩባንያዎች እና 16 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዘንድሮው የህንድ አፍሪካ ኤክስፖ በኢትዮጵያ የተካሄደው እንደ ሀገር ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የተከናወኑ ስራዎችን ውጤታማነት በመመልከት መሆኑን ተናግረዋል።

ኤክስፖው በአገር ውስጥ በአይሲቲ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት፤ ህንድ በዲጂታል ስርዓተ ምህዳር የደረሰችበትን ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑን አመላክተዋል።

ወጣቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ከሚፈጥራቸው ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማሰልጠንን ጨምሮ ምቹ መደላደል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት በዘርፉ የፈጠራ ውጤቶች ያላቸው ግለሰቦችን በገንዘብ እንዲሁም ቴክኒካል ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት መሰንበት ሸንቁጤ የምክር ቤቱ አባላት በኤክስፖው ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው፤ በእውቀት ሽግግር በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ግንኙነትን በማጠናከር እንዲሁም ተሞክሮዎችን በመቅሰም በኩልም ተስፋ የተጣለበት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሸትኪንቶንግ ኢትዮጵያና ህንድ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የህንድ ኢንቨስተሮች በአፍሪካ በአይሲቲ እና በንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው አመላክተዋል።

ዛሬ የተከፈተው ኤክስፖ የኢትዮጵያና የህንድ ኩባንያዎች በአይሲቲና ሌሎችም ዘርፎች አብሮ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የህንድ ባለሀብቶች ለ75 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመው፤ ህንድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው የተናገሩት።

የህንድ-አፍሪካ የአይሲቲ ኤከስፖ ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ በኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ሩዋንዳ እና ጋና በእያንዳንዱ ሀገራት ለሁለት ዓመታት መካሄዱን በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ መረጃ ያሳያል።

ህንድ በቴሌኮሙኒኬሸን ኔትወርክ የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ኤምባሲው በመረጃው ጠቅሷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም